የክልል መንግስታት በጸጥታ ጉዳይ መግለጫ እንዳይሰጡ ታገዱ
(ኢሳት ዜና የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ለሁለተኛ ጊዜ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የአዋጁን ተግባራዊነት ከሚከታተለው እዝ ውጭ ማንኛውም የክልል ባለስልጣን በክልሉ ስላለው የጸጥታ ሁኔታ ምንም አይነት መግለጫ መስጠት እንደማይችል አግዷል። ከዚህ ቀደም የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የኮሚኔከሽን ሃላፊዎች እንዲሁም የዞን የጸጥታ ባለስልጣናት ሳይቀሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሚወስዱት እርምጃ ላይ መግለጫዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል። የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ፣ የምስራቅ ኦሮምያ፣ የአምቦና የአርሲ ክልል ባለስልጣናት መከላከያ ሰራዊቱ በህዝቡ ላይ የሚወስደውን እርምጃ አውግዘው መግለጫ ሰጥተው ነበር። ብአዴንም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፣ መካለከያ ሰራዊቱ በሰሜን ወሎ ዞን የወሰደውን እርምጃ የሚኮንን መግለጫ ሰጥቷል። አዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአሁን በሁዋላ የትኛውም የክልል ባለስልጣንም ሆነ ድርጅት የጸጥታውን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ መከላከያ በሚወስደው እርምጃ ላይ አስተያየት መስጠት አይችልም በማለት፣ የክልል ባለስልጣናትን መብት ሙሉ በሙሉ አግዷል።
ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ፣ የትራንስፖርት ሂደትን ማወክ ፣ በትምህርት ተቋማት፣ በስፖርት ማዘወተሪያዎችና ሌሎችም አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዲሁም የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዝውውር ማገድ በአዋጁ ተከልክሏል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ማስፈጸሚያዎች ላይ ተቃውሞን ማሰማትና መረጃን ማሰራጨትም ተከልክሏል። የመሰረት ልማት እና ኮማንድ ፖስቱ በለያቸው የኢንቨስትመንት አካባቢዎች ከሰአት እላፊ ውጭ ሲንቀሳቀሱ በተገኙትም ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አዋጁ መብት ይሰጣል።
ይህን አዋጅ የአሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት፣ የእንግሊዝ መንግስትና የጀርመን መንግስታት መቃወማቸው ይታወቃል። የአሜሪካ መንግስት ያወጣውን ጠንካራ መግለጫ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቃውመው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርን መጠየቃቸው ታውቋል።