የኬንያ ገዢ ፓርቲ ህገወጥ ኢትዮጵያውያንና የዩጋንዳ ተወላጆችን በቀጣይ ነሃሴ ለሚካሄደው ምርጫ ድምፅ እንዲሰጡ እየመዘገበ ነው ተባለ

ኢሳት(ጥር 16 ፥ 2009)

የኬንያ ገዢው ፓርቲ ህገወጥ ኢትዮጵያውያንና የዩጋንዳ ተወላጆችን በሃገሪቱ በነሃሴ ወር ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ድምፅ እንዲሰጡ እየመዘገበ መሆኑን የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት  አጋለጠ።

የተቃዋሚ ጥምረቱ መሪ ራይላ ኦዲንጋ የሃገራቸው ብሄራዊ የስለላ አገልግሎት የድምፅ መመዝገቢያ ወረቀቶችን ወደ ሁለቱ ሃገራት በማጓጓዝ ለኢትዮጵያውያንና የዩጋንዳ ተወላጆች የኬንያ መታወቂያ እየሰጠ  እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ማድረጋቸውን ዘስታንዳርድ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

የፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግስት የፊታችን ነሃሴ ወር በሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዢውን መንግስት ለመጣል ጥምረት መመስረታቸው ይታወሳል።

ይሁንና የኡሁሩ ፓርቲ ምርጫው ላይ ተፅዕኖን ለማሳደር በህገወጥ ድርጊት መሰማራቱንና ኢትዮጵያውያንን እና የዩጋንዳ ተወላጆችን ድምፅ እንዲሰጡ እየመዘገበ መሆኑን የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል።

የኬንያ መንግስት እየፈጸመ ላለው ለዚሁ ህገወጥ ምዝገባ በቂ ማስረጃ አለን ያሉት ራይላ ኦዲንጋ የሃገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት አገልግሎት ኢትዮጵያውያኑ እና ዩጋንዳውያኑ የኬንያ መታወቂያ ወረቀት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

ገዥው የሃገሪቱ ፓርቲ ከወራት በኋላ በሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ላይ ተጽዕኖን ለማሳደር ሲል በተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶች ተሳታፊ ሆኖ መቀጠሉን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ገልጸዋል።

የፊታችን ነሃሴ ወር በኬንያ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ የሃገሪቱ ዜጎች ምዝገባን እያካሄዱ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ሆነች ኬንያ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ለቀረበው ቅሬታ የሰጡት ምላሽ የለም።

ከዚህ በፊት የኬንያ የፓርላማ አባላት የሃገሪቱ የደህንነት አባላት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከለላ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለኢትዮጵያ አሳልፈው ይሰጣሉ ሲሉ ቅሬታን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ለእነዚሁ የደህንነት ሃላፊዎችና አባላት ከፍተኛ ገንዘብ ሲከፍል መቆየቱንም የኬንያ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ሲዘግቡ ቆይተዋል።