የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ 98 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸነፉ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010) የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያለተቀናቃኝ በተካሄደው የሀገሪቱ 2ኛ ዙር ምርጫ 98 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸናፋቸውን የምርጫ ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ አደረገ።

ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉት የቅርብ ተፎካካሪው ራይላ ኦዲንጋ ነገ መግለጫ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

በነሐሴ ወር በተካሄደው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፈጠሩ በተባሉ ቴክኒካል ችግሮች ምርጫው እንዲደገም ከውሳኔ ላይ መደረሱ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም አሸናፊነታቸው የተሰረዘባቸው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለዳግም ምርጫው ፈቃደኛ በመሆን በሂደቱ ውስጥ ቀጥለዋል።

የቅርብ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ በምርጫ ኮሚሽኑ መዋቅር ላይ እንደገና ጥያቄ በማንሳት በሂደቱ እንደማይሳተፉ በመግለጻቸው በሀገሪቱ እንደገና ረብሻ መከተሉም አይዘነጋም።

የምርጫ ኮሚሽኑ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ምርጫውን ዳግመኛ ለማካሄድ ሲወስን ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው በምርጫው እንዳይሳተፉና በቤታቸው እንዲወሰኑ ጥሪ አቀረቡ።

በነሀሴ ወር ከተካሄደው ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ከመራጩ ሕዝብ ከግማሽ በላይ ባልተገኘበትና 39 በመቶ ያህል ብቻ በተሳተፈበት ምርጫው እንዲካሄድ ተደርጓል።

የራይላ ኦዲንጋ የድጋፍ መሰረት ናቸው በተባሉ 25 የምርጫ አካባቢዎች ከረብሻ ስጋት ጋር በተያያዘ ምርጫው አልተካሄደም።

በምርጫው ከተሳተፉት መራጮች ውስጥ የ98 በመቶ መራጮችን ድምጽ በማግኘት ዛሬ ማሸነፋቸው የተገለጸው ኡሁሩ ኬንያታ ለቀጣዮቹ 5 አመታት ለሁለተኛ ዙር ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ራይላ ኦዲንጋ ነገ የሚሰጡት መግለጫ ምን እንደሚያስከትል የታወቀ ነገር የለም።

ከኬንያ ምርጫ ጋር በተያያዘ እስካሁን 50 ሰዎች መገደላቸውም ታውቋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ምርጫውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ምርጫው ነጻ፣ፍትሃዊና ታአማኒ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።