የካናዳ ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ላይ ግፊትን እንዲደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፓርላማ አባላቱ ጋር ለመወያየት ጥያቄ አቀረበ

 

ኢሳት (ጥቅምት 25 ፥ 2009)

የካናዳ ፓርላማ አባላት የሃገራቸው መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ግፊትን እንዲያደርግ በቅርቡ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፓርላማ አባላቱ ጋር ለመወያየት ጥያቄን አቀረበ።

አሌክሳንደር ኖቴል የተባሉ የካናዳ የፓርላማ አባላት በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

የፓርላማ አባሉ በፓርላማ ያቀረቡት ንግግር መነጋገሪያ እየሆነ መምጣቱን ለኢሳት የገለጹት ምንጮች ድርጊቱን ተከትሎ በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና በአሌክሳንደር ኖቴል በኩል ውይይት እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረቡን መረጃዎች በመስጠት አስረድተዋል።

በፓርላማ ንግግርን ካቀረቡት ሚስተር ኖቴል በተጨማሪ የፓርላማ አባል የሆኑት ሚስተር ፒተር ኬንት፣ ለሃገራቸው መንግስት የጹሁፍ ደብዳቤን በማቅረብ ካናዳ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ መጠቀሚያ በማድረግ ጫናን እንድታሳድር አሳስበዋል።

በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ወደ 2 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሱት የፓርላማ አባሉ፣ የካናዳ መንግስት ማንኛውንም መንገድ በመጠቀም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

ካናዳ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ሁለገብ ድጋፍ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እንዲሁም ነጻነት እንዲሰፍን የሚያግዝ መሆን ይኖርበታል ሲሉ የፓርላማ አባሉ ፒተር ከንት ለሃገራቸው መንግስት ባቀረቡት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

የፓርላማ አባላቱ በኢትዮጵያ ይፈጸማል ያሉትን ኢሰብዓዊ ድርጊት በአደባባይ መናገር መጀመራቸውን ተከትሎ ድርጊቱ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቅሬታ ማሳደሩን ምንጮች ለዜና ክፍላችን አስረድተዋል።

በኦታዋ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚኒስትር ኮንስለር (ነቢያት ጌታቸው) በኩል ባቀረበው ጥያቄ በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና በፓርላማ አባሉ አሌክሳንደር ኖቴል በኩል ውይይቱ ቀጣዩ ሳምንት እንዲካሄድ ሃሳቡን አቅርቧል።

ይሁንና የፓርላማ አባሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽን ይስጡ አይስጡ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ኤምባሲው ቅሬታን ካቀረቡት የፓርላማ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ባለስልጣናትም ለማግባባት እየሞከረ መሆኑን ምንጮች አክለው አስረድተዋል።

በቅርቡ የካናዳ የፓርላማ አባላት የሃገራቸው መንግስት በኢትዮጵያ በሽብርተኛ ወንጀል ክስ ውሳኔ ተላልፎበት የሚገኝ ካናዳዊ ለማስለቀቅ ጠንካራ ዕርምጃን እንዲወስድ ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።