የካናዳ መንግስት አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አስቸኳይ አዋጁን በማንሳት፣ እስረኞችን በመፍታት ሁሉን አቀፍ ለውጦች እንዲያደርጉ ጠየቀ

የካናዳ መንግስት አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አስቸኳይ አዋጁን በማንሳት፣ እስረኞችን በመፍታት ሁሉን አቀፍ ለውጦች እንዲያደርጉ ጠየቀ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ/ም) መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የካናዳ ኤምባሲ የአዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድን ሹመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ለሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምኅዳሩን በማስፋት መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ በመፍታት፣ ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች ተሳታፊና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ሊረጋገጡ ይገባልያለው የካናዳ መንግስት፣ አሁን ሊደረግ የታሰበው የለውጥ ተሃድሶና የስልጣን ሽግግር ገቢራዊ ለማድረግ አስቸኳይ አዋጁን ማንሳትና ከሁሉም ያገባናል ከሚሉ ባለድርሻ አካላት ጋር አሳታፊ የሆነ ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጿል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገራቸው የጠራ ርዕይ ሰንቀው የሚያደርጉትን ሰላማዊውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ገቢራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ነጻ የሆኑ ገለልተኛ የብዙሃን መገናኛዎች ነጻነት ሊከበሩ እንደሚገባና ሁሉን አሳታፊ የለውጥ ተሃድሶ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ የካናዳ መንግስትና ሕዝብ እንደሚያግዝ አስታውቋል።