ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው ኩዊንስ ኮሌጅ በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ባሳደረባቸው ጫና ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን ገለጹ። ኮሌጁንም ወደ ሌላ ሰው በማስተላለፍ የ25 አመት ልፋታቸው ከንቱ መቅረቱን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምስረታ ሂደት ውስጥ ከመጀመሪያ ጀምሮ ተሳታፊ መሆናቸውን የገለጹት የኩዊንስ ኮሌጅ መስራችና የቀድሞ ባለቤት አቶ ታደለ ሺበሺ ሲደረግባቸው የነበረውን ጫና መቋቋም ባለመቻላቸው 17 አመታት የተገነባውን ኮሌጅ በ1.5 ሚሊዮን ብር ወደ ሌላ ሰው ለማስተላለፍ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
ኮሌጁን የተረከበው ሰው ስልጣን ላይ ካሉት ወገኖች ጋር አካባቢያዊ ቅርበት ስላላቸው ማነቆው ተወግዶ፣ ኮሌጁ የሚስፋፋበትን ሁኔታ መከተሉን አብራርተዋል።
በአጠቃላይም 17 አመታት የደከሙበትና ከሶስት ሺ በላይ ተማሪዎች ያስመረቀውን ኮሌጅ ሲያጡ አዕምሯቸው እስከመነካት መሄዱንና በህክምና መፈወሳቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
ሃገራቸው ገብተው መዋዕለ-ንዋይ የሚያፈሱ ኢትዮጵያውያን አቅም ከገነቡ በኋላ የሚደርስባቸውን ጫና ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ያስታወሱት አቶ ታደለ ሺበሺ፣ ሁሉም ከእኛና ከሌሎቹ ሊማር ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመመስረት ግንባት ቀድም የሆኑት የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ባለቤትና ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ደረሰብኝ ባሉት ጫና ዩኒቨርስቲውን ለሼህ መሃመድ አላሙዲን ሸጠው መሰደዳቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ ግንባር ቀደም የሆነው የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ባለቤትና ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ዳኛቸው ይልማም በተመሳሳይ ከሃገር መሰደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።