ግንቦት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በምእራብ ጎጃም ዞን በቡሬ ከተማ ንብረትነቱ የሼህ ሙሀመድ አላሙዲን የሆነው የቡሬ ኩል ውሀና ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ መርዛማ ዝቃጭ በጤና ላይ እያደረሰው ያለ ችግር አሳስቦናል ሲሉ የወረዳው ኗሪዎች ተናገሩ፡፡
ህዝቡ ለመጠጥና ለመስኖ ስራ በሚገለገልባቸው ይስርና ኩል ወንዞች የሚለቀቀው መርዛማ ዝቃጭ ወንዙን ተከትሎ በሰፈረው ህዝብ ላይ ከሚያደርስው የጤና ችግር ባለፈ በንብረት ላይ አሉታዊ ተፅንኦ ፈጥሯል ያሉት ኗሪዎቹ ፣ ጉዳዩን ለከተማ አስተዳድሩ ብናሳውቅም ምንም ዓይነት መፍትሔ አላገኘንም ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ሳይንሳዊ የቆሻሻ አወጋግድ ስልትን የማይጠቀም ከመሆኑ ባሻገር ችግሩን ለመቅረፍ ምንም ዓይነት ጥረት እያደረገ አይደለም ያሉት ኗሪዎቹ ጉዳዩ በቀላሉ መታየት የሌለበት ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣናቱን በገንዘብ ተፅንኦ ከጎኑ ያሰለፈው የቡሬ ኩል ውሀና ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ የህዝቡን የካሳና ሌሎች ጥያቄዎች ማፈን ችሏል ያሉት አንድ በወንዙ መስኖ ተጠቃሚ ማህበር አባል የሆኑ አዛውንት በውሀው አመድ የለበሰ ገላቸውን እያሳዩ ለማን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶናል ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
መርዛማ ዝቃጭ ቀጥታ በሚለቀቅበት ወንዝ ያመረትነው ምርት ሊበከል ይችላል በሚል ስጋት ኗሪዎች ምርታችንን ሊገዙ ባለመቻላቸው ለምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ዳርጎና ሲሉ አዛዉንቱ ጨምረው ተናግረዋል፡፡