(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2010)
አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 7 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ አመራሮች ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑን የፌደራል አቃቢ ሕግ አስታወቀ።
በዚሁም መሰረት አቶ በቀለ ገርባ፣ጉርሜሳ አያና፣አዲሱ ቡላላ፣ደጀኔ ጣፋ፣ጌቱ ጋሩማ፣ተስፋዬ ሊበንና በየነ ሩዳ ክሳቸው ተቋርጧል።
የእነ አቶ በቀለ ገርባ ክስ በዚህ መልኩ ተቋርጧል ቢባልም በፍርድ ቤት ችሎት መድፈር በሚል ሁለት ጊዜ የ6 ወራት እስር ስለተወሰነባቸው ከእስር ቤት የመውጣታቸው ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
የእነ አቶ በቀለ ገርባ ክስ ተቋረጠ የተባለው በኦሮሚያ ክልል መላው አካባቢ የስራ ማቆም አድማና ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ነው።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/አመራሮች ክሳቸው ተቋርጦ ከእርስ ይለቀቃሉ ሲባል ቢቆይም ፍርድ ቤት በማመላለስ ይንገላቱ ስለነበር ተቃውሞአውቸውን በችሎት ሲያሰሙ ቆይተዋል።
አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የኦፌኮ አመራሮች ችሎት ውስጥ ዘምራችኋል፣ በዳኛ ስትጠሩ ከመቀመጫችሁ አልተነሳችሁም በሚልም ሁለት ጊዜ የ6 ወራት እስራት ቅጣት ተጥሎባቸዋል ከእስር የመለቀቃቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኖ ነበር።
ከኦሮሚያው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ከአገዛዙ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የተሰማው ዜና ግን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 7 የኦፌኮ አመራሮች ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በዚሁ መሰረት ክሳቸው የተቋረጠው የኦፌኮ አመራሮች አቶ በቀለ ገርባ፣ጉርሜሳ አያኖ፣አዲሱ ቡላላ፣ደጀኔ ጣፋ፣ጌቱ ጋሩማ፣ተስፋዬ ሊበንና በየነ ሩዳ ናቸው።
እነዚሁ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጧል ቢባልም በችሎት መድፈር ሁለት ጊዜ የ6 ወራት እስራት ስለተፈረደባቸው ከእስር የመውጣታቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።
አገዛዙ ከእስር እንዲወጡ ከፈለገ ተከሳሾቹ ፍርደኞችም በመሆናቸው አንድም በይቅርታ ወይንም በምህረት ሊለቀቁ ይገባል።
ስለዚህ ጉዳያቸው ወደ ይቅርታ ቦርድና ወደ ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት መመራቱን ከጠቅላይ አቃቢ ሕግ የተገኘው መረጃ እንደሚያመልክት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።