(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 12/2009)ዶክተር መራራ ጉዲናን ወክሎ ክሱን ለአፍሪካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ማእከል ይህንን አህጉራዊ ተቋም ለምን መረጠ የክሱ ፋይዳስ ምን ሊሆን ይችላል ብዙዎች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።
የኢትዮጵያ የሰብአዊና የዲሞክራሲያዊ እድገት ማእከል አደራ ጠባቂና ጠበቃ የሆኑት ዶክተር አባድር ኢብራሂም ለኢሳት እንደገለጹት ክሱን ለዚሁ ተቋም የተመረጠው ኮሚሽን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አያያዝ ጉድለት የሚያሳስበውና በጉዳዩ ላይም ተከታታይ መግለጫዎችን ያወጣ በመሆኑ ነው። ተሰሚነቱም ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የተሻለ እንደሆነም ዶክተር አባድር ያስረዳሉ
የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መራራ ጉዲናን በመወከል ለአፍሪካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ክሱን ያቀረበው የኢትዮጵያ የሰብአዊና የዲሞክራሲያዊ እድገት ማእከል በ3 ፍሬ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ይገልጻል።ምንም እንኳ ዶክተር መራራ ለክሱ መነሻ ቢሆኑም የአሽቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎችም ሆነ ከህገመንግስቱ ጋር የሚጻረር ነው በሚልም ህጉንና አፈጻጸሙን ይሞግታል።በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በደቡብ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎም የመነግስት ታጣቂዎች የወሰዱት የሃይል እርምጃም በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ኮሚሽኑ ግፊት እንዲያደርግም ይጠይቃል።
ዶክተር መራራ ጉዲና ከታሰሩ በኋላ የተፈጸመባቸው ኢሰብአዊ አያያዝም ተገቢ እንዳልሆነና ትኩረት እንዲደረግበት ማእከሉ በክሱ ላይ አመልክቷል።
ዶክተር አባድር ኢብራሂም እንዳሉትም በኢትዮጵያ ያለውና የፍትህ ስርአት መፈተሽ ችግሩን በጉልህ ለማሳየት ይረዳል።እናም ማእከሉ ክሱን ሲያቀርብ ትኩረቱን በዚህም ላይ አድርጓል ብለዋል።
የአፍሪካ የሰብአዊና የህዝቦች መብት ኮሚሽን በአፍሪካ ቻርተር አማካኝነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1987 በአዲስ አበባ የተመሰረት ነው።
መቀመጫውም በጋምቢያ መዲና ባንጁል መሆኑ ይታወቃል። ይህ አህጉራዊ ተቋም በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በማጋለጥ የተለያዩ ሪፖርቶችን አውጥቷል።በተለይም በአማራና በኦሮሚያ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸው የሃይል እርምጃዎች እንዳሳሰበው ሲገልጽ ቆይቷል።ተቋሙ በመንግስት ታጣቂዎች የተገደሉትና የታሰሩት ሰዎች ሁኔታ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በመጠየቅ መግልጫ እስከማውጣት ደርሷል።ዶክተር አባድር እንደገለጹት የክሱን ሂደትና ውጤት በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ለህዝብ በየጊዜው ይፋ የሚደረግበት ሁኔታ ይመቻቻል። እናም ሕዝቡ ክሱን ያቀረበውን ማእከል በሙያና በምክር እንዲሁም በገንዘብ በመደገፍ እንዲተባበር ዶክተር አባድር ጥሪ አቅርብዋል።