የኦዴግ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2010) የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/አመራሮች እነ አቶ ሌንጮ ለታ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ።


ከመንግስት ጋር ድርድር መጀመሩን ከሳምንት በፊት በመግለጫ ያስታወቀውየኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/አመራሮች በአቶ አባዱላ ገመዳ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ጉዟቸውን በተመለከተም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በሃገር ቤት ፓርቲያቸውን በሕጋዊነት ለማስመዝገብ ወይንም ከሌሎች ጋር ተዋህዶ ለመስራት ሁኔታዎችን እንደሚያጤኑም ገልጸዋል።
የትጥቅ ትግል ዲሞክራሲን አያመጣም ያሉት የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ሌሎችም የነሱን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከመንግስት ጋር የተነጋገሩት ወደ ሃገር በሚገባበት ሁኔታ ላይ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ድርድር አለመጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የኦዴግ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው ከነአርበኞች ግንቦት 7 ጋር የፈጠሩትን ሃገራዊ ንቅናቄ በተመለከተ ለተነሳባቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።ሌሎችም ወደ ሂደቱ እንዲገቡ ድልድይ መሆን እንችላለን ብለዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት የኦዴግ አመራሮች ሊቀመንበሩ አቶ ሌንጮ ለታ፣ምክትል ሊቀመንበሩ ዶ/ር ዲማ ነጎ እንዲሁም የአመራር አባላቱ ዶ/ር በያን አሶባ ፣አቶ ሌንጮ ባቲ እና ዶ/ር ሃሰን ሁሴን ናቸው።