የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማይቀበለው አስታወቀ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማይቀበለው አስታወቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ገዥው ፓርቲ አስቸኳይ አዋጁን ያጸደቀበት ሁኔታ የሕግ አግባብን ያልተከተለ በመሆኑ እንደማይቀበለው አስታውቋል። በመላው ኢትዮጵያ ለተካሄደውን ሕዝባዊ አመጽ ምላሽ ለመስጠት ገዢው ፓርቲና አጋሮቹ የአገራችንን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ጥልቅ ተሃድሶ አካሄድን ካሉ በኋላ፣ የፖለቲካ እስረኞችን እንፈታለን፣ የእስረኞች ማሰቃያ ማእከል የሆነውን ማእከላዊ እስር ቤትን እንዘጋለን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ቃል እንገባለን ማለታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፣ ሕዝባችንና ፓርቲያችን ጥሩ ጅምር መሆኑን ከግንዛቤ በመውሰድ ገዢው ፓርቲ የገባውን ቃል ያከብራል ባለበት ወቅት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ቃሉን በማጠፍ አስቸኳይ አዋጅ በማወጅ የኮማንድ ፖስት አስተዳደር በማቋቋም አስተዳደሩን ወታደራዊ አድርጎታል ብሎአል። አስቸኳይ አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ በሌለበት ወቅት እንዲታወጅ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑንም ኦፌኮ አስታውቋል።
ውሳኔው ሕግና ሕገመንግስቱን የጣሰ በመሆኑ እንደማይቀበለውና አዋጁ በአሁኑ ወቅትም ሰላምና መረጋጋትን በአገርቱ አላማምጣቱን ኦፌኮ ጠቅሷል።
ኦፌኮ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የህገ መንግስት ጥሰትን ለሚመለከተው የህግ አካላት ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በህዝባችን ላይ የተጫነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማንቀበል መሆኑን እንዲታወቅና ህዝባችንም በዚህ አዋጅ መገዛት እንደሌለበት እናስገነዝባለን ብሎአል።
ህዝቡ የጀመረውን ህጋዊና ሰላማዊ የፍትህና ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ባልተቆራረጠ አኳኋን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበው ኦፌኮ፣ ከዚህ አዋጅ ጋር ተያይዞ ለተከሰቱትና እየተከሰቱ ላሉት የህግ ጥሰትና የዜጎች ጉዳት ኢህአዴግና የኢህአዴግ መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲል ኦፌኮ ገልጿል።