የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አንድነት እንዲመጡ ጥሪ ቀረበ

ኢሳት (ህዳር 5 ፥ 2009)

በአትላንታ የተካሄደው የኦሮሞ መሪዎች ጉባዔ በማህበረሰቡ ዙሪያ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አንድነት እንዲመጡ ጥሪ በማድረግ የአቋም መግለጫ አወጣ።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከህዳር 11 እስከ ህዳር 13 በአትላንታ ከተማ የተካሄደው የኦሮሞ መሪዎች ጉባዔ ህዝቡ የህወሃትን አገዛዝ ለማስወገድ የሚያደርገውን ትግል እየደገፉ ያሉ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ስለሚልቅ ወደ አንድነት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ጉባዔው በአራት ሰነዶች ላይ ተወያይቶ  የማሻሻያና የማዳበሪያ ሃሳቦችን በመቀበል መጠናቀቁን ከስብሰባው በኋላ የወጣውን የአቋም መግለጫ አመልክቷል።

ሰነዶቹ በምን ላይ ያተኮሩ ስለመሆናቸውና ስለይዘታቸው ግን በዝግ ከተካሄደ በኋላ የወጣው የኦሮሚያ የመሪዎች ጉባዔ የጋራ መግለጫ ያለው ነገር የለም።

በኦሮሚያ የዛሬ አመት በግንጪ ከተማ የተከሰተውን እና መላውን ኦሮሚያ ያደረሰውን የህዝብ ትግል የተጀመረበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ የተካሄደው ጉባዔ በህወሃት አገዛዝ ህይወታቸውን ለከፈሉት ሰማዕታት የህሊና ጸሎት አድርጓል።

በአገዛዙ የስቃይ ሰለባ የሆኑትና በየማጎሪያው የታሰሩት እንዲሁም የተሰደዱት የኦሮሞ ተወላጆችንም አስቧል።

ጉባዔው በትግሉ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ኦሮሞዎች የሚደግፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት ለማቋቋም መወሰኑንም መግለጫው አመልክቷል።

ከዚህም ሌላ የኦሮሞ ምርምርና የህዝብ ማሳወቂያ ማዕከል ለመመስረት ጉባዔው መስማማቱንም ተገልጿል። ጉባዔው በኢትዮጵያ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያና እስር በማውገዝ መላው የአገሪቱ ህዝብ በአንድ ላይ እንዲቆምና የአገዛዙን የከፋፍለህ አስተዳደር እንድያስወግድ ጥሪ አቅርቧል።