(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2010)
የኦሮሞ ሕዝብ ለምን ተበደለ፣ጥቅምስ ለምን ቀረበት በሚል ኦቢኤን ቴሌቪዥን መዘገቡ አግባብ አይደለም ሲሉ የብሮድካስት ባለስልጣን አቶ ዘርአይ አስገዶም ገለጹ።
አቶ ዘርአይ የክልልና የግል መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች በተገኙበት መድረክ እንዳሉት ቴዲ አፍሮ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ ሲያውለበልብ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ በፌስቡክ ገጻቸው ድጋፍ ሰጥተዋልም ብለዋል።
የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ ኦቢኤን በድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳ በኩል ወጣቶች ቤተመንግስት እንዲገቡ ቅስቀሳ ተደርጓል በሚል መተቸታቸውም ይታወሳል።
የክልልና የግል መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ጽሕፈት ቤት አመራሮች ግን ብሮድካስት ባለስልጣን ጣቱን በሌሎች ላይ ከሚቀስር ራሱን እንዲፈትሽ ጠይቀዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሕወሃቱ ነባር ታጋይ አቶ ዘርአይ አስገዶም የኦሮሞ ሕዝብ በደልና አለመጠቀም በመገናኛ ብዙሃን ሊተላለፍ አይገባም ብለዋል።
እናም ይህንኑ መልዕክት ያስተላለፈው የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ /ኦ ቤ ኤን/ ስህተት ሰርቷል ሲሉ አቶ ዘርአይ ሃላፊዎቹን በዛቻ ወርፈዋል።
እንደ አቶ ዘርአይ አባባል የአማራ ክልል በበኩሉ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት መነሻ በማድረግ ከኮብ የሌለበትን ባንዲራ በኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ሲስተጋባ ነበር ሲሉ ዛቻ የተመላበት ማስፈራሪያ ሰንዝረዋል።
የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ግን በአቶ ዘርአይ አስገዶም የቀረበባቸውን ትችት አልተቀበሉም።
በኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ/ኦ ቢ ኤን/ ላይ የቀረበውን ትችት አስመልክተው ማስተባበያ የሰጡት የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወካይ አቶ ፈቃዱ ተኮማም እውነትን መሰረት አድርገን መዘገባችን ትክክል ነበር ብለዋል።
አቶ ዘርአይ አስገዶም በድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳ በኩል ወጣቶች ወደ ቤተመንግስት እንዲገቡ ቅስቀሳ ተደርጓል በሚል ትችት ማቅረባቸው ይታወሳል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሸገር ሬዲዮ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ጠፍታበት ፍለጋ ላይ ነው፣የአሁኗ ኢትዮጵያ ደስ አላለችውም በሚልም መተቸታቸው አይዘነጋም።
የሕወሃቱ ነባር ታጋይ አቶ ዘርአይ አስገዶም በክልልና በግል መገናኛ ብዙሃን ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የተሞላበት ትችት ቢሰነዝሩም የመድረኩ ተሳታፊዎች ግን ጉዳዩን ባለመቀበል ከዚህ ይልቅ ብሮድካስት ባለስልጣን ራሱን ይፈትሽ ብለዋል።