የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት፤ የኦሮሞ ህዝብን ነጻነት ሳያጎናጽፍ በጦርነት ኣዋጅና ማስፈራሪያ ወደኋላ አይመለስም” ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አስታወቀ።

መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኦነግ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤የኦሮሞ ህዝብ ከአራት ወር በላይ ሲያደርገው በቆየው የጭቆና ፍጻሜ ኣመጽ ፤ተፈጥሮኣዊውንና በኣለምኣቀፍ ህግ ያለውን መብቱን ከማስከበር ውጪ ለሌሎች ህዝቦች ኣንዳችም ጥላቻ እንደሌለው፣ ይልቁንም ለሁሉም ህዝቦች መብቶች መከበር ፍላጎት ያለው መሆኑን በማያወላዳ ሁኔታ ለመላው ዓለም በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ተጨቋኝ ህዝቦች አስገንዝቧል ብሏል።
የህዝቦች ጠላት የሆነው አገዛዝ የኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ የጀመረውን ትግል ሌላ ኣቅጣጫ ለማስያዝና ጸረ-ሰላም እንደሆነ ኣድርጎ በማቅረብ ስም ለማጥቆር ያደረገው ጥረት በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦችም ሆነ የስርዓቱ ኣጋር ባዕዳን ዘንድም ተቀባይነት እንዳላስገኘለት ግንባሩ አመልክቷል።
“ዘላቂ ሰላም ለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ይገኛል” በሚል ርእስ ግንባሩ ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤እውነታን በመካድ በሌላው ላይ ጣት መቀሰር የማያዋጣ መሆኑን የተገነዘበው የወያኔ መንግስት ፤ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጦርነት ኣውጆ ክልሉን በኮማንድ ፖስት ለመምራት መወሰኑን በመዘንጋት፤ ከሰሞኑ በይስሙላው ፓርላማ በኦሮሚያ ለደረሰው ጥፋት ስህተቱ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እንደሆነ በግልጽ አውጇል ብሏል።
“የወያኔ መንግስት እዚህ የደረሰው የህዝቦችን ጥያቄዎች በሃይል በማፈን፣ በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር ኣብረውና ተባብረው እንዲይታገሉ በማድረግ መሆኑ ሁለም የሚያውቀውና የሚገነዘበው ሃቅ ነው።” ያለው ኦነግ፤ ዛሬ ህዝቦች በጠላት ሴራ ላይ ከመንቃታቸው የተነሳ “ጭቆና ይብቃ!፣ ለዝንተ-ዓለም በማይሟላ ተስፋ እየተዋሸን ኣንኖርም!” ብለው በኣራቱም የሃገሪቷ ኣቅጣጫ የኣንገዛም-ባይነት ኣመጻቸውን እያፋፋሙ ይገኛሉ” ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማፘም ደሳለኝ፡ሰሞኑን ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት ችግሩ ከመልካም እጦት አስተዳደር የመነጩ እንደሆነ መጥቀሳቸውን ያወሳው የኦነግ መግለጫ፤”የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሞበጃቸውን ራሳቸው የሚያውቁና የነቁ መሆናቸውን ኃይለማርያም ገና አሁን መገንዘቡ የሚደንቅ ነው” ይላል።
“የኦሮሞ ሕዝብ ራሴን ማስተዳደር አለብኝ ብሎ መብቱን በመጠየቁ እየታፈነና እየተገደለ ነው ያለው ኦነግ፤ “ኢትዮጵያን አንቆ ለያዘው ችግር ምክንያቱ መልካም አስተዳደር ማስፈን ያልቻለው የወያኔ ስር ዓት ብቻ ነው” ብሏል።
“ኦሮሚያን በ8 ዞኖች ከፋፍሎ በሳሞራ ዩኑስ በሚመራው የጦር ኣስተዳደር ስር ማስገባቱ መልካም ኣስተዳደርና ሰላምን ኣያስገኝም።”የሚለው የግንባሩ መግለጫ፤ኦሮሚያን ለወታደራዊ አገዛዝ አሳልፎ መስጠት ችግሩን ይበልጥ እንደሚያባብሰው አስጠንቅቋል።
“የኦሮሞ ሕዝብ በወያኔ አልገዛም፤ ተላላኪው ኦፒዲኦም አይወክለኝም” በማለቱ ሕዝቡን ለማፈን ተብሎ በስምንት ዞኖች በተዋቀረው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ውስጥ ለይስሙላ እንኳ አንድም የኦሮሞ ተወላጅ የጦር መኮንን አለመኖሩን ኦነግ በመግለጫው ዘርዝሯል።
ኣመጹ ከተጀመረ ኣንስቶ በጦር እየታመሰ ያለው የኦሮሚያ ግዛት፤ በተለይ ካለፈው የካቲት 26 ወዲህ ኣስተዳደሩ በኢህኣዴግ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለጦር ሰራዊቱ በመሰጠቱ፤ በኮማንድ ፖስቱ የተካተቱት ጄኔራልች እስከ ቀበሌ በዘረጓቸው መዋቅራቸው ትዕዛዝ እየተገዛ እንደሚገኝ ግንባሩ ገልጿል።
“የሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግርም ሆነ በኦሮሚያ ተዘርግቶ ስራ ላይ እየዋለ ያለው ወታደራዊ መዋቅር፤ ወያኔ ኣሁንም የሃገሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ኣለመሆኑን በሚገባ ያሳያል”ያለው ኦነግ፤ በተለይ ደግሞ ኦሮሚያን በጦር ኣስተዳደር ስር ማስገባትና እርምጃ እንወስዳለን በማለት ያሰማው ዛቻ በኦሮሞ ህዝብና በኦነግ ላይ ያወጀውን ጦርነት በድጋሚ ማደሱን የሚያስገነዝብ እንጂ ሌላ ትርጉም የሚኖረው ኣይሆንም”ብሏል።
“ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ መብት ሙሉ በሙሉ እስከሚከበር ድረስ እያካሄዱት ያለውን ፍልሚያ ይቀጥላሉ።” ያለው ኦነግ፤ “ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት የኦሮሞ ህዝብን ነጻነት ሳያጎናጽፍ በጦርነት ኣዋጅና ማስፈራሪያ ወደኋላ የማይመለስ መሆኑን ለወዳጅም-ለጠላትም እናረጋግጣለን” ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።