የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ወታደሮች 3 የአጋዚ ወታደሮችን ገደሉ

የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ወታደሮች 3 የአጋዚ ወታደሮችን ገደሉ
(ኢሳት ዜና የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘዋ ጣፎ ከተማ ላይ ትናንት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች 3 የአጋዚ ወታደሮችን መግደላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ፖሊሶቹ ቀን ላይ አብረው በጥበቃ ላይ እንደነበሩ የገለጹት ምንጮች፣ ምሽት ላይ የደንብ ልብሳቸውን በመቀየርና ሲቪል ልብስ በመልበስ 3 ወታደሮችን ገድለው ተሰውረዋል። ድርጊቱን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር እንዲሰፈር ተደርጓል። ድርጊቱን የፈጸሙትን ለመያዝ በሚል የአካባቢው ወጣቶች ታፍሰው ተወስደዋል።
በዚሁ አካባቢ በሚገኘው ድልድይ አቅራቢያ አንድ ቦንብ ፈንድቶ አንድ መምህር ቆስሎ ሆስፒታል መግባቱንም ምንጮች ገልጸዋል።
በአጋዚ ወታደሮችና በኦሮምያ ፖሊስ አባላት መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ አለመግባባቱም የጦር መሳሪያ እስከማማዘዝ እየደረሰ መሆኑን የሚደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።