(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 15/2011)በኦሮሚያ ክልል በግድያ፣በዘረፋና በገንዘብ ስርቆት ላይ ተሰማርተው በነበሩ ሃይሎች ላይ ርምጃ ለመውሰድ የጸጥታ አካላት መሰማራታቸውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በሌላም በኩል ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘ ተሳታፊ የሆኑ 15 ያህል ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ ክልል ጸጥታ የሚያውኩና በስም ያልተጠቀሱት አካላት 12 ፖሊስና 29 ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸውን አስታውቀዋል።
በፖሊስ ጣቢያዎችና በመንግስት ተቋማት ላይ በፈጸሙት ዝርፊያ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወስደዋል።
2ሺ 700 ያህል የጦር መሳሪያዎችንም ዘርፈዋል።
እነዚህ አካላት ጸጥታ እያወኩና ዘረፋ እየፈጸሙ የሚገኙት በወለጋ፣በኢሉአባቦራ፣በቡኖ በደሌና በደቡብ ኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን መሆኑንም ከኮሚሽነሩ አለማየሁ እጅጉ መግለጫ መረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚሁ በኦሮሚያ ክልል”አባ ቶርቤ” በሚል ስያሜ ግድያና ዘረፋ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ 15 ግለሰቦች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
እነዚህ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግልሰቦች በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበራቸውም ተመልክቷል።
ግለሰቦቹ አዲስ አበባ የመሸጉት ከፍተኛ ባለስልጣናትን፣ታዋቂ ግለሰቦችንና አክቲቪስቶችን ለመግደል እንደሆነም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
ግለሰቦቹ በተያዙበት ወቅትም ሽጉጥና ቦምብን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እንደተገኙባቸው ይፋ ሆኗል።