የኦሮሚያ ክልል ከስልጣን የለቀቁትን ፕሬዚዳንቱን ለማሳከም ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱ ታወቀ

የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ያለፉትን ሶስት የሥልጣን አመታት በህክምና ያሳለፉትና ከሳምንት በፊት በገዛ ፈቃዳቸው ከሃላፊነታቸው የተሰናበቱት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳን ለማሳከም ክልሉ ከአንድ ሚሊየን አሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉ ተሰማ፡፡

በጰጉሜ ወር 2002 ዓ.ም ኦህዴድ ባካሄደው ጉባዔ ባልተጠበቀ መንገድ አቶ አባዱላ ገመዳን ተክተው ወደስልጣን የመጡት አቶ አለማየሁ በስራ ገበታቸው ላይ ብዙም ሳይሰነበቱ በመታመማቸው ያለፉትን ሶስት ዓመታት በህክምና ምልልስ ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡

አቶ አለማየሁ አቶምሳ፤ የአቶ አባዱላ ገመዳ አመራር የተዘፈቀበትን ስር የሰደደ ሙስና ለመታገል በተሾሙ ማግስት በትኩስ ጉልበት ተነሳሽነት አሳይተው እንደነበር የጠቆሙት የኢሳት የኦሮምያ ምንጮች፣ በሁዋላ ግን ከምግብ መመረዝ ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ህመም በመዳረጋቸው ስራ ለመስራት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በአቶ አባዱላ የክልል አመራር ዘመን የአዲስአበባ አጎራባች የሆኑ የኦሮሚያ ከተሞች ከፍተኛ የመሬት ወረራ ወይም ሙስና የተፈጸመ ሲሆን አቶ አባዱላ ይህን ለማስቆም ምንም ጥረት አለማድረጋቸው ብቻም ሳይሆን እሳቸውም ተዋናይ ሆነው መገኘታቸው በመተካካት ስም በኦህዴድ ውስጥ ያላቸው ሚና እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

አቶ አለማየሁ የክልል ፕሬዚደንት በመሆናቸው በመንግስት ወጪ መታከማቸው ተገቢና ሕግ የሚደግፈው ቢሆንም፣ ለእሳቸው ሕክምና ባለፉት 3 ዓመታት የወጣው ወጪ በኢህአዴግ በትረ ስልጣን ዘመን ለማንም ወጥቶ እንደማያውቅ ታውቋል።

አቶ አለማየሁ ተከታታይ ሕክምናቸውን በታይላንድ ያካሄዱ ሲሆን በከፍተኛ ስፔሻሊስት ሀኪሞች የሚደረግላቸው ክትትል ለአንድ ጊዜ ከ200 እስከ 400 ሺ ብር የሚገመት ወጪ ያስወጣል።

ለአቶ አለማየሁ የወጣው አንድ ሚሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ደሃ ህዝቦች ከአንድ በላይ የጤና ጣቢያዎች ወይም ት/ቤቶችን መገንባት የሚችል መሆኑን በመግለጽ በዚህ መልኩ የሕዝብ ገንዘብ መውጣቱ ትልቅ የሐብት ብክነት ተደርጎ ተቆጥሯል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱን ለመተካት የኦሮምያ ባለስልጣናት ሽኩቻ ውስጥ መግባታቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ በምክር ቤቱ የተሾሙና ተጠሪነታቸውም ለምክር ቤቱ ቢሆንም ፣ ምክር ቤቱ ሳያውቀው እንዲወርዱ ተደርጓል። እስካሁንም ድረስ የምክር ቤቱ አባላት ማን እንደሚሾም የሚያውቁት ነገር የለም።