የኦሮሚያ ክልል በህወሀት ሞግዚትነት እየተመራ ነው

ሚያዚያ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-ክልሉ በአሁኑ ጊዜ እየተመራ ያለው በርዕሰ መስተዳድሩ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ሳይሆን፤ በህወሀቱ አቶ ገብረተንሳይ ወልደተንሳይ ነው።

በሕዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በህወሀት ሞግዚትነት እየተመራ ያለው፤ የኦህዴድ ባለሥልጣናት ሀላፊነታቸውን መወጣት ስላልቻሉ ነው ተብሏል።

  ክልሉ በህገ መንግሥትና በህዝብ ተወካዮች ህግ መሰረት ክልላዊ የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅር እንዳለው ይታወቃል።

  ይሁንና ፍኖት የተቀሳቸው የመረጃው ምንጮች እንዳሉት፤ በየደረጃው የተቀመጡት ባለሥልጣናት በሙስና በመዘፈቅ፣ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ በመወሰን፣በቡድን በመደራጀት ወደ

ተለያየ አቅጣጫ በመጓተት አለመግባባት ጎልቶ በመታየቱ፤ የሞግዚት አስተዳደሩ ተፈፃሚ ሊሆን ግድ ብሏል፡፡

 እነዚህ ምንጮች፦“የክልሉ ፕሬዝዳንት አጀንዳ ለማስያዝ የማይችሉበት ሁኔታዎች አሉ”ሲሉም ያክላሉ።

ይሁንና በሞግዚት አስተዳደሩ ያልተስማሙ የኦህዴድ አባላት፤”የክልላችን አስተዳደር፤ ከክልላችን ውጪ ባለ ግለሰብ የበትዕዛዝ እየተመራ ነው፡፡” በማለት ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

 እንደ ዜናው ምንጮች ከሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ ክልሉን የሚመሩት የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት የኦህዴዱ  አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሳይሆኑ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት

ውስጥ መቀመጫ ያላቸው የህወሀቱ  አቶ ገ/ተንሳይ ወ/ተንሳይ  ናቸው።

  ህወሀት ለሁለት ከመከፈሉ በፊት አቶ ሰለሞን ተስፋዬ  ወይም በቅጽል ስማቸው ሰለምን ጢሞ የሚባሉት የቀድሞ የህወሀት ባለስልጣን፤ ኦህዴድ ጽ/ቤት ውስጥ ቢሯቸውን ከፍተው የድርጅቱንና የክልሉን የመንግሥት አመራር እግር በእግር እየተከታተሉ በመገምገም አመራር ሢሰጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

 ህወሀት ለሁለት በተከፈለ ሰሞን አቶ መለስ የክልል ፕሬዚዳንቶችንና አመራሮችን ሰብስበው ፦” ከእንግዲህ በክልላችሁ ላይ እናንተ ተመልከች፤ሌላው ፈትፋች የሚሆንበት ጊዜ አብቅቷል”  በሚል ቃል በማማለል፤ በክፍሉ ጊዜ  ከእርሳቸው ጎን እንዲወግኑ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

አቶ መለስ ለክልሎቹ አመራሮች ያለፈው የተበላሸ አሠራር እንደማይደገም ቃል ቢገቡም፤ ወንበራቸው በተደለደለ ማግስት የሞግዚት አሰራሩ በስፋት ቀጥሏል።

 ያኔ ሰለሞን ጢሞ በ ጽህፈት ቤታችን ውስጥ ቢሮ ከፍተው ነበር የሚያስተዳድሩን፤ አሁን ደግሞ አቶ ገ/ተንሳይ ወ/ተንሳይ ቢሮአቸውን ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ውስጥ አድርገው ከዚህ በፊት ሰለሞን ጢሞ ሢሰሩ የነበረውን ሥራ ተክተው እየሠሩ ነው” ብለዋል- ኦሮሚያ ዳግም ለህወሀት በሞግዚትነት በመሰጠቱ የተበሳጩ የ ኦህዴድ አባላት።

በአሁኑ ጊዜ  በክልሉ ውስጥ ተደማጭነትና ተቀባይነት ያለው፤ የክልሉ ፕሬዘዳንት ትዕዛዝና መመሪያ ሳይሆን የአቶ ገ/ተንሳይ መመሪያና ትዕዛዝ ነው”ሲሉም አክለዋል-እነዚህ የ ኦህዴድ አባላት።

  በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ፕሬዝዳንት የአቶ አለማየሁ አቶምሳንና የአቶ ገ/ተንሳይ ሐሳብን ለማካተት የተደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide