(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 4/2010) በውጭ የሚገኙ በኦሮሞ ስም የተደራጁ ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት ገብተው በሰላም እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ስም የተደራጁ ሌሎች አካላት የኦሮሚያን ክልል ሰላም ለማደፍረስ በመስራት ላይ መሆናቸውን አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ይህንን የተናገሩት እየተካሄደ ባለው የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።
አቶ ለማ መገርሳ ለኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት (ጨፌ) አባላት በሰጡት ማብራሪያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በኦሮሞ ስም የተደራጁና መቀመጫቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረጉንና ብዙዎችም መግባታቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ በግለሰብም ሆነ በቡድን በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ አካላት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አመልክተዋል ።
ይህ ሁኔታም በተጨባጭ በኦሮሚያ ክልል በምዕራቡ ክፍል መታየቱንም አስታውቀዋል።
በዚህም በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንዲሁም ዘረፋ መፈጸሙን አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ይህንን እንዲከላከል ጥሪ ያቀረቡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትም ከተግባራቸው የማይቆጠቡ ከሆነ፥ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ይገደዳል ሲሉም አሳስበዋል።