(ኢሳት ዲሲ–ጥር 1/2010)
በወልዲያ ከነማና በዋልዋሎ እግር ኳስ ቡድን መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ግጭት ማስከተሉ ታወቀ።
ግጭቱ የተከሰተው ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሲሆን በፖሊስና በኳስ ደጋፊዎች መካከል ከተከሰተ መለስተኛ ግጭት ባለፈ የከፋ ጉዳት አለመድረሱም ታውቋል።
የወልዲያ እግር ኳስ ቡድንና የትግራይ ክልሉ ዋልዋሎ የእግር ኳስ ቡድን የሚያደርጉት ጨዋታ ከሁለቱ ክልሎች ውጪ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የተወሰነው በክልሎቹ የሚካሄደው ውድድር ግጭት በማስከተሉ እንደሆነም ታውቋል።
በትግራይና በአማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚካሄዱ ውድድሮች በተደጋጋሚ ግጭት ማስከተላቸውም ይታወሳል።
በአዲግራት የተፈጸመው ግድያ በመላ ሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ በማስከተሉ 20 ያህል ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸው ምስተጓጎሉ ይታወቃል።
ይህ በእግር ኳስ ሜዳና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተከሰተ ያለው ብሔረሰብን መሰረት ያደረገ ግጭት እንዲቆም የሃይማኖት አባቶች በጋራ ጥሪ ማቅረባቸውን ማስታወስ ተችሏል።
ባለፈው ግንቦት በባህርዳር ከነማና በመቀሌ ከነማ መካከል በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ውድድር ከፍተኛ ግጭት ማስከተሉ ሲታወቅ በቅርቡ በወልዲያ ከነማና በመቀሌ ከነማ መካከል በወልዲያ ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ያስከተለው ግጭት በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ለተማሪዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በክልሎቹ የሚከሰተውን ግጭት ለመሸሽ በአዲስ አበባ ከተማ ያዘጋጀው የወልዲያና የወልዋሎ ቡድን ጨዋታ ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች መካከል ስታዲየም ውስጥ የነበረው ውዝግብ ከስታዲየም ውጪም ቀጥሏል።
ፖሊስ ውዝግቡን ለመፍታት ሲንቀሳቀስ ግጭቱ ከፖሊስ ጋር መቀጠሉም ታውቋል።
በዚህም ፖሊስ እስከ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ድረስ ሲያባርራቸው የሚያሳይ በምስል የተደገፈ መረጃም ተሰራጭቷል።
በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት ግን የታወቀ ነገር የለም።