ሚያዝያ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ እና የጋራ ብልጽግና ጽ/ቤት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጓቸውን ማንኛውንም ጉዞዎች ለደህነታቸው አስጊ እና አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ያላቸውን አካባቢዎች ለይቶ አሳውቋል።
የቱሪስት መስህብ ከሆኑት ደብረዳሞ እና የሃ በስተቀር ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር 10 ኪሎ ሜትር አካባቢ በሚገኙት ከአክሱም እስከ አዲግራት ባሉ ዋና መንገዶች ዜጎቹ እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል። በሱዳን እና ኬንያ ድንበር 10 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በሚገኙ ከተማዎች እና አውራጎዳናዎች ላይ የጉዞ እገዳ ወጥቶባቸዋል። ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን በሚያዋስናት 10 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ እና በኢትዮ-ሶማሊያ ድንበር አካባቢዎችም የተከለከሉ የጉዞ መስመሮች ተለይተው ታውቀዋል።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር አዋሳኝ የሆኑት የኒጎቦ የቀድሞው ፊቅ፣ ጃራር፣ የቀድሞው ደጋሃቡር፣ ሸበሌ የቀድሞው ጎዴ፣ በቆራሄ እና ዶሎ የቀድሞው ዋርዴር የደህንነት ስጋት ቀጠናዎች ተብለዋል።
ኢትዮጵያን ከሶማሌ እና ከኬንያ በሚያዋስናት 100 ኪሎ ሜትር በሚሸፍኑት የአፍዴር እና ሊበን ዞኖች ለጉዞ የተከለከሉ ዞኖች ተብለዋል። በጋንቤላ ክልል የሚገኙ በኑዌር ዞን የሚገኙት የአኮቦ፣ ዋንታዎ፣ ጂካዎ እና ላሬ ወረዳዎች እና በአኝዋክ ዞን የሚገኘው የጆሬ ወረዳ የጉዞ ደህንነት ዋስትና የሌላቸው አካባቢዎች ተብለው እገዳው ውስጥ ተካተዋል።
በሰሜን ጎንደር የጸገዴ፣ ምእራብ አርማጭሆ እና ታች አርማጭሆ፣ በጅጅጋ ከተማ፣ በደቡብ ሱዳን ወሰን በአኝዋክ ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ዲማ፣ ጎሬ፣ ኢታንግ እንዲሁም በጋንቤላ የዱር እንስሳት ጥበቃ አገልግሎት አካባቢ እንዳይጓዙ ሲል ማስጠንቀቂያዊ ምክር ሰጥቷል።
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ተስፋፍቶ የነበረው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ጋብ ያለ ቢመስልም ዳግም የታፈነው አመጽ ሊያገረሽ ይችላል ሲል እንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ እና የጋራ ብልጽግና ጽ/ቤት (The Foreign and Commonwealth Office) አሳስቧል። ዜጎቹ ከጉዞዋቸው አስቀድመው የኢትዮጵያን የዜና አውታሮች መስማት እንዳለባቸው እና የጉዞ ወኪሎችን ምክር እንዲጠይቁም አሳስቧል።
አፕሪል 25 ቀን 2017 እ.ኤ.አ. ጎንደር ዲቻቱ ሆቴል ላይ በደረሰ የቦንብ አደጋ አንድ የውጭ አገር ዜጋን ጨምሮ 5 ሰላማዊ ዜጎች መቁሰላቸውን የዜና አውታሮች ዘግበዋል። በተመሳሳይ በጎንደር ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ላይ አፕሪል 1 ቀን 2017 እ.ኤ.አ. በደረሰ የቦንብ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተጎድተዋል። ከጃንዋሪ ወር 2017 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በጎንደር እና ባሕርዳር ከተሞች ሁለት የተለያዩ ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተከስተዋል።
በመላው ኢትዮጵያ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚደረጉ የጉዞ ማእቀቦች ቢነሱም በአሁኑ ወቅት ቱሪስቶች እና የውጭ ዜጎች የሚጎበኟቸው አካባቢዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በመሆኑም ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መናሃሪያዎች፣ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች፣ ባሮች፣ የአምልኮ ቦታዎች፣ እንዲሁም የሃይማኖት እና የስፖርት ዝግጅቶች ላይ እንዳይገኙ አስጠንቅቋል።
በተለይም በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አዋሳኝ የሆኑት አካባቢዎች የድንበር ውጥረቱ እያየለ በመምጣቱ የሽብር ጥቃትን ጨምሮ እገታዎች ሊፈጸሙ ይችላል ሲል የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ እና የጋራ ብልጽግና ጽ/ቤት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ከእንግሊዝ መንግስት በተጨማሪ በቅርቡ የአሜሪካ መንግስትም ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ይታወቃል።