ነሃሴ ፲፫ ( አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን በእብናት ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች የወረዳው ባለስልጣናት የጠሩትን ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል። ባለስልጣናቱ በስፍራው ለተገኙ የንስሃ አባቶች በእየቤቱ እየዞሩ መንፈሳዊ ልጆቻቸውን እንዲመክሩ፣ የእስልምና አባቶችም ተመሳሳይ ሚናቸውን እንዲወጡ ቅስቀሳ ሲጀምሩ፣ ህዝቡ “እናንተ ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ ባቀረብን ወታደር አምጥታችሁ አስገደላችሁን ፣ ከኢህ በሁዋላ ከእናንተ ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም” በሚል በአንድ ድምጽ ስብሰባውን ረግጦ በመውጣቱ ስብሰባው ተበትኗል።
ከፍተኛ ፍጥጫ በታየበት በዚህ ስብሰባ ወጣቶች የመስተዳድሩን ባለስልጣናት ሲነቅፉ ታይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ የይፋት ተወላጆች በትናንትናው እለት የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ከፖሊሶች ጋር መጠነኛ ግጭት ተፈጥሮ የተወሰኑ ወጣቶች ተጎድተዋል። በዚሁ ከተማ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ተቃውሞ ወጣቶች መገደላቸው ይታወቃል።
በአዲስ ዘመን ደግሞ የገበሬ ታጣቂዎች እና የወረዳው ባለስልጣናት ተቃውሞ ያሰሙትን የመንግስት ሰራተኞች ማሰር የጀመሩ ሲሆን፣ ከህዝብ ጎነ ቆሟችሁዋል ያሉዋቸውን ታጣቂዎች ደግሞ መሳሪያቸውን ለማስወረድ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የከተማውና የገጠሩ ህዝብ እንዳይገናኝ ለማድረግ፣ “ቤተክርስቲያናችሁን የሚያቃጥሎ ጸጉረ ልውጦች ወደ አካባቢያችሁ ገብተዋልና አካባቢያችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል ቅስቀሳ በመቀስቀስ፣ የገጠሩ ህዝብ ለገበያ ወደ ከተማ እንዳይገባና ከከተማው ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ ከፍተኛ የቅስቀሳ ስራ እየተሰራ ነው። ባለፉት ሶስት ወናት ገጠሩ ወደ ከተማ የሚያደርገው የንግድ እንቅስቃሴ የተቋረጠ ሲሆን፣ ይህን የቅስቀሳ ስራ የሚሰሩ ሰዎች በቀን 70 ብር እየተከፈላቸው በገጠሩ ህዝብ ላይ ሽብር እየለቀቁ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እሁድ የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በከተማው ከፍተኛ ውጥረት ይታያል፡፡ በአንዋር መስጂድ ዛሬ ከፍተኛ ፍተሻ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ህዝቡ በእሁዱ ሰልፍ ወደ አደባባይ እንዳይወጣም በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።