ሚያዚያ ፲፫(አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሕገወጥ መንገድ የታንዛኒያን ድንበር አቋርጣችሁ ገብታችኋል ተብለው በታንዛኒያ ፍርድ ቤት የተበየነባቸውን የእስር ጊዜያት ያጠናቀቁ 74 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በታንዛኒያና ኬንያ ድንበር ታቬታ በምትባል የድንበር አዋሳኝ ስፍራ ላይ ተጥለዋል።
የታንዛኒያ መንግስት በገባችሁበት በኬንያ ተመለሱ በማለት ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ ከሕግ ውጪ ስደተኞቹን ከግዛቱ ሲያባርር፣ የኬንያ መንግስት በበኩሉ ስደተኞቹ የእስር ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ወደ ትውልድ አገራቸው መላክ ሲገባቸው ወደ ኬንያ መመለሳቸው አግባብ አለመሆኑን በመቃወም ወደ ግዛቴ አይገቡም በማለት ስደተኞቹ ከማከሰኞ እለት ጀምሮ በታቬታ ድንበር ላይ አስታዋሽ አጥተው ለስቃይ ተዳርገዋል።
የኬኒያ የስደተኞች ጉዳይ ምክትል ኮሚሽነር ሄንሪ ዋፉላ ፣ ”የታንዛኒያ ባለስልጣናት ስደተኞቹን ቀጥታ ወደ አገራቸው መመለስ ነበረባቸው። እነሱ ግን ወደ ኬንያ መላክን መርጠዋል። እኛ ደግሞ መልሰን ወደ ታንዛኒያ ልከናቸዋል ይሄ በሕግ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው” በማለት የታንዛኒያ ባለስልጣናትን ድርጊት ኮንነዋል።
የታንዛኒያ መንግስት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግን በመተላለፍ ኢሰብዓዊ ድርጊት በኢትዮጵያዊን ስደተኞች ላይ ፈጽሟል። እስካሁን ድረስም ስደተኞቹን ለመታደግ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩንም ስታንዳርድ ዲጅታል አክሎ ዘግቧል።