(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 5/2011)የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አስመራ ተመለሱ።
ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ በሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነት ላይ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ እንጂ በአንዳንድ ወገኖች እንደሚባለው ከኦነግ ጋር ለማሸማገል አይደለም ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ለኢሳት ገልጸዋል።
ቅዳሜ ማለዳ አዲስ አበባ የገቡት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን በቲውተር ገጻቸው የጻፉት የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ስለጉዞው አላማም አብራርተዋል።
ሐምሌ 2 ቀን 2010 አስመራ ላይ ሁለቱ ሃገራት የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ርምጃዎችን ለመገምገምና በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አዲስ አበባ መግባታቸውን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋም ለኢሳት በሰጡት ቃለ ምልልስ በሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነት ላይ ለመነጋገር ፕሬዝዳንቱ መግባታቸውን አመልክተዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመሸምገል ኢትዮጵያ ገቡ በሚል የሚነሳው ሃሳብም ሃሰት መሆኑን ተናግረዋል።
ጉዟቸው በሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነት ላይ ያተኮረ እንደሆነም ለኢሳት አብራርተዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የምረቃ ስነስርአት ላይ የተገኙ ሲሆን በአርባ ምንጭና በጅማ ከተሞች ቆይታ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ አስመራ ተመልሰዋል።