የኤሌክትሪክ ታሪፍ መጨመር የዋጋ ንረት ማስከተሉ አይቀርም ተባለ

ኢሳት (ጥቅምት 24 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ኤለክትሪክ አገልግሎት ታሪፍን ከ 50 በመቶ በላይ ለመጨመር መወሰኑ ከተጠቃሚው ህዝብና ባለሀብቶች ተቃውሞ እንደገጠመው ተገለጠ።

አገልግሎቱ ለበርካታ አመታት በመንግስት ድጎማ መቆየቱን የገለጸው የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ ሀይል መስሪያ ቤት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ወጪውን የሚሸፍን ታሪፍ በማስፈለጉ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጭማሪ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ አድርጓል።

በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ለአመታት ያህል ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የነበረው የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎችና የፋብሪካ ባለቤቶች 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉ አገልግሎቱን ለማግኘት ፈተና እንደሚሆንባቸው በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ሀገሪቱ አስተማማኝና የ24 ሰአት አገልግሎት ማግኘት ባልጀመረችበት ወቅት ከእጥፍ በላይ የታሪፍ ዋጋ መውሰን አግባብ እንዳልሆነም ነዋሪዎች ገልጸዋል ።

ይኸው በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የዋጋ ማስተካከያ ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዘንድም ቅሬታ ማስነሳቱ ታውቋል።

የማህበሩ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ፋሲል ታደሰ መንግስት የፋ ያደረገው የታሪፍ ጭማሪ ” ሙት ማለት ነው” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት መግለጻቸውን ከሀገር ቤት የተገነው መረጃ አመልክቷል። የኤሊክትሪክ ታሪፍ ጭማሪውን ተከትሎም በበርካታ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ተመሳሳይ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችልና መንግስት ጉዳዩን በአግባቡ መመልከት እንዳለበት ነዋሪዎችና ባለሀብቶች አሳስበዋል።

የሀገሪቱ የኤለክትሪክ ታሪፍ ዝቅተኛ መሆን ሀይል አምርተው ለመንግስት ለመሸጥ ፍላጎት ያላቸውን ኩባንያዎች እያሸሸ እንደሚገኝ የኤለክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ አስታውቀዋል።

ኩባንያዎቹ ከመንግስት ጋር የሚያደርጉት ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የዋጋ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉን ሀላፊዋ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ አለም አቀፍ የቢዝነስ ጉባኤ መግለጻቸውን ለመረዳት ተችላል።

በአሁኑ ወቅትም 14 የውጭ ኩባንያዎች የአኤለክትሪክ ሀይልን በማመንጨት ለመንግስት በሽያጭ ለማቅረብ ድርድርን እያካሄዱ እንደሚገኝ ታውቋል።