ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)
በተያዘው አመት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከአምስት በመቶ በላይ መቀነሱንና ድርጊቱ በውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገለጠ።
መንግስት ለተለያዩ ድርጅቶች ልዩ የማበረታቻ ድጋፍን በመስጠት የውጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም የተገኘው ውጤት ግን እጅግ አነስተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቀዋል።
የሃገሪቱ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ በማስመልከት ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርትን ያቀረበው ሚኒስትሩ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የውጭ ንግድ ገቢው በ5.5 በመቶ ማሽቆልቆሉን አመልክቷል።
በተለይ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማግኘት ጠብቃቸው በነበሩ የጨርቃ-ጨርቅና የቆዳ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የገቢ ማሽቆልቆል መመዝገቡንና ችግሩም የቴክኖሎጂ አቅም አለመገንባት እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ አህመድ አብተው ለተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።
መንግስት 103 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማምረት አቅዶ የ53 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ብቻ መመረታቸውንም ሚኒስትሩ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተካሄደን ጥናት ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል።
በተያዘው አመት ከውጭ ገቢ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ በመሆኑም በሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ መጠበቁን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስተድተዋል።
ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማቱ በበኩላቸው፣ የገቢያ እጦት በማጋጠሙ ምክንያት የታሰበው የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ አለመቻሉንና ምርቶቻቸውን ለሃገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
የንግድ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ልዩ ድጋፍ ተሰጥቷቸው በቂ የውጭ ምንዛሪ ባላስገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንደሚጀምርም በማሳሰብ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።