ኢሳት (ጥር 15 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ያለፉት አምስት ወራቶች የኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ማስመዝገቡ ተገለጸ።
መንግስት ከዘርፉ ወደ 279 ሚሊዮን ዶላር ኣካባቢ ለማግኘት እቅድን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በአምስት ወራቶች ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ግን 166 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለመንግስት መገኛኛ ብዙሃን አስታውቋል።
ጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ገቢን አስመዝግበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ወደ 90 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ገቢን ለማግኘት እቅድ ቢኖረውም ከዘርፉ ሊገኝ የቻለው ግን ወደ 46 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑ ታውቋል።
በኢንዱስትሪ ውጭ ንግድ ላይ የተመዘገበው ዝቅተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሏል።
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ ገቢ ከታሰበው በታች ሆኖ መገኘቱ ሃገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ መሆኗን የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
የአለም ባንክ በበኩሉ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ንግድ ገቢን ለማነቃቃት ብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ መጠን ዝቅ እንድታደርግ የመንግስት ባለስልጣናት የቀረበውን ሃሳብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት ሳይቀበሉት ቀርበዋል።
ይሁንና በተያዘው አዲስ አመትም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየት ላይ በመሆኑ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ፈተና ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የግብርና አቅርቦት ማነስ፣ የአስተዳደራዊና የቴክኒክ ድጋፎች ማነስ፣ ጥራትና ተያያዥ ችግሮች በኢንዱስትሪ እንዲሁም በአጠቃላይ በውጭ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደሩ ነው ከተባሉ ችግሮች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በሃገሪቱ የተከሰተውን የፋይናንስ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ሲባል መንግስት በቅርቡ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ ወዳጅ ናቸው የተባሉ የባህረ ሰላጤ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።