የኢንተርኔት አጠቃቀም አዋጅ ጸደቀ

ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2008)

በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን ያደርጋል ተብሎ ከተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ትችት ሲቀርብበት የቆየውና የኮምፒውተር ወንጀል ለመደንገግ የቀረበው አዋጅ ማክሰኞ ጸደቀ።

የኢትዮጵያ መንግስት የረቂቁ የኢንተርኔት የስለላ ቁሳቁሶችን እንደሚጠቀም መረጃዎች ቢቀርቡበትም ሃገሪቱ የኮምፒውተር ወንጀል ጥቃት እየሆነ መጥታለች ሲሉ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።

ማክሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዲሱ አዋጅ፣ ግለሰቦች ለአመፅ ያነሳሳሉ የተባሉ የፎቶና የቪዲዮ ምስሎችን ከመለዋወጥ የሚከለክል ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን ድርጊቱ የሰብዓዊ መብትን የመረጃ ነጻነትን የሚጋፋ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በፓርላማ የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገብረ-እግዚያብሄር አርአያ የጸደቀ አዋጅ የግለሰብ መብቶችን የሚጋፋ አይደለም ሲሉ ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ ገልጸዋል።

የረቂቅ አዋጁ መውጣትን ተከትሎ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች አዋጁ ግለሰቦች የሚያደርጓቸውን የመረጃ ልውውጦች ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የስነ-ልቦና ጫናን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ሃገሪቱ የኢንተርኔት ወንጀል ጥቃት መሆን በመጀመሯ ምክንያት ወንጀሉን ማፅደቁ አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቋል።

ይሁንና በዚሁ ድርጊት ስለተፈጸሙ ጥቃቶችና ስለደረሱ ጉዳቶች መንግስት የሰጠው ዝርዝር መርጃ የሌለ ሲሆን፣ ጎረቤት ሃገራት ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው አለበት ሲል በቅርቡ መግለፁ የሚታወስ ነው።

በርካታ የማስታወቂያ የኢሜይል መልዕክቶችን የላኩ ግለሰቦች ሳይቀር በአዋጁ ተጠያቂ እንደሚሆኑን የእስር ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው በዚሁ አዋጅ ተንደንግጓል።

ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን፣ ምስሎችንና የቪጂዮ መረጃዎችን ያሰራጩ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በአዋጁ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን መንግስት በግለሰቦች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እንደሚያጠናክር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።