የኢንተርኔት አገልግሎት መታፈኑን ተከትሎ በርካታ መስሪያ ቤቶች ችግር አጋጥሟቸዋል

ግንቦት ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አገራቀፍ ፈተናዎችን ምክንያት በማድረግ ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው የኢንተርኔት አፈና ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ ባንኮች፣ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ስራቸውን ለማከናወን ተቸግረዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ደርጅቶች እንዲሁም ኢንትርኔት በስልካቸው የሚጠቀሙ፣ ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ድርጅቶች ሁሉ ስራቸው እንደተስተጓጎለባቸው ወኪላችን ገልጿል።
በተለያዩ የመንግስት ና የግል ድርጅቶች እንዲሁም የንግድ ተቋማት ላይ የደረሰውን ኪሳራ ለማወቅ ጊዜው ገና ቢሆንም፣ ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስራቸውን የሚሰሩ ድርጅቶች ገቢያቸው እንደሚቀንስ አክሎ ገልጿል።
የኢንተርኔት አፈናው ለምን ያክል ቀናት እንደሚቆይ አልታወቀቀም ። ይሁን እንጅ ቢቢሲ አንድ የህዝብ ግንኙነት ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የ12ኛ ክፍል ፈተና በመጪው ሳምንት የሚሰጥ በመሆኑ የኢንተርኔት አፈናው ሊቀጥል ይችላል።
አምና ፈተና መሰረቁን ተከትሎ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ ሲያጋጥማት ፣ ገዢው ፓርቲም ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሰራ ደርሶበት ነበር። በዚህ አመት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
ገዢው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠረው ኢትዮቴሌ አማካኝነት በመላ አገሪቱ ኢንተርኔት ሲዘጋ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ቀድም በአገሪቱ የነተሱ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ የኢንተርኔት አጋልግሎት ለ2 ጊዜ ያክል ተቋርጦ ነበር።
ገዢው ፓርቲ ኢንተርኔት ያፍናል በሚል በተደጋጋሚ ይቀርብበት የነበረውን ክስ ሲያስተባብል ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትችቶች ወደ ጎን በማለት አፈናውን በገሃድ ማመን ጀምሯል።