የኢንሳው ዳይሬክተር ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ መስሪያ ቤቱ ትርምስ ውስጥ ነው
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) ለኢሳት የደረሰው ጥቆማ እንደሚያመለክተው የዶ/ር አብይ አህመድን ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ በመቃወም ጄ/ል ተክለብርሃን ወ/አረጋዊ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በሁዋላ መስሪያ ቤቱ ትርምስ ውስጥ መግባቱን ምንጮች ገልጸዋል።
የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲው በአቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዲመራ መደረጉ ያበሳጫው የህወሃት ባለስልጣናት፣ የህወሃት የስለላ አባላት ዋና ዋና የሚባሉ የስለላ መሳሪያዎችን ወደ መቀሌ እያጓዙ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል። ዋና ዋና የሚባሉ የህወሃት ሰላዮች ወደ ውጭ አገራት የወጡ ሲሆን፣ የተወሰኑ የስለላ መሳሪያዎች እንዲወድሙ ሌሎች ደግሞ እየተሰረቁ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል። የስለላ ተቋም ዋና አዛዥ ሻለቃ ቢኒያም ተወልደም የስልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸው ታውቋል። 30 የሚሆኑ የስለላ ሰራተኞች በእስራኤል አገር አቮርኒጋ ቴክኖሎጂ ኩባንያ አማካኝነት የስለላ ስራ ትምህርት እየወሰዱ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመስሪያ ቤቱን ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።