(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2011) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የኢኒጂነር ታከለ ኡማ ሹመት የነዋሪው ውክልና የሌለው ነው በሚል የሚነሱ አስተሰሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው ሲል የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባልተለመደ ሁኔታ ስለ መዲናይቱ ከተማና በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ አንዳንድ ወገኖች በህግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የህዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ብሏል፡፡
እናም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡ፣ በህጋዊ መንገድ በተመረጠው አስተዳደር ላይ አመጽ የሚያነሳሳ እንቀስቃሴ ህገወጥ ድርጊት እና ፀረ-ህገመንግሥት ስለሆነ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲል አስጠንቅቋል።
ከምክር ቤቱ የምርጫ ዘመን ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም መወስኑን መግለጫው አስታወሷል።
ሰኔ 30/ 2010 ዓ.ም. የከተማውን አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995ን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ መሠረትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፡- የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ መሆኑንም ነው ያመለከተው።
እናም ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራላይ ያለው ምክር ቤቱ እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደሩ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል” በሚል በተደነገገው አዋጅ መሠረት ህጋዋ እውቅና አግኝቶ የቀጠለ አስተዳደር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።
ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”ተብሎ በግልጽ መቀመጡንም አስታወሷል።
የከተማው ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የከተማውን ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ሹመት በወቅቱ በተገኙት ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ መጽደቁንም መግለጫው አስታወሷል፡፡
ይህም ሆኖ ግን “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊም አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው ሲል መግለጫው አሳስቧል ።
አንዳንድ ወገኖች በህግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ የህዝብ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የህዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ብሏል የአዲስአበባ ምክር ቤት መግለጫ፡፡
እናም ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎችን በመታገል ከአስተዳደሩና ከምክርቤቱ ጐን በመሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ አድርጉ ሲል ለከተማዋ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ የሁላችንም ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆንዎ ታውቆ ከከተማው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የህጐች ሁሉ የበላይ በሆነው ህገመንግሥት ምላሽ የሚያገኝ ስለሆነ የግጭት መንስኤ መሆን አይገባውም ብሏል።