የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚቴ መንግስት ለሱዳን አሳልፎ የሰጠው እጅግ ሰፊ መሬት ህገወጥ ነው አለ

ግንቦት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የድንበሩ ኮሚቴ ከፍተኛ አካል የሆነው ምክር ቤት ግንቦት 10 እና 11 ቀን 2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠበብቶች የተሳተፉበት ታላቅ ጉባዔ በሲሊቨር ስፕሪንግ ከተማ፣ ሜሪላንድ፣ አሜሪካ  አካሂዶ ባወጣው መግለጫ የሻለቃ ቻርልስ ጉዊን ድንበር ከለላ መሥመር ሕገወጥ መሆኑን በተጨባጭ ውድቅ አድርጓል።

 

መንግስት ለሱዳን በስጦታ ያስረከበው ዳር- ድንበራችን የኢትዮጵያ መሬት መሆኑን የገለጸው  ኮሚቴው ፣  የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፤ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ ልትጠይቀው የምትችል ሰፊ ለም መሬት እንዳላት ጥናቶች ማመለከታቸውን ጠቅሷል።

 

ጉባኤው ያዘጋጀው ታሪካዊ ሠነድ በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ እንደተጠናቀቀ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስታውቅ ኮሚቴው ገልጿል።

 

ለወደፊቱ የሀገራችንን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያስከብር፤ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲመጣ፤  ለሱዳን የተሰጠውን የሀገራችንን ምዕራባዊ ዳር-ድንበር ለማስመለስና ለማስጠበቅ ይህን ሠነድ ከሌሎች ጥናቶች ጋር አያይዞ ሊጠቀምበት እንደሚችልም ኮሚቴው አስታውቋል።