ጥቅምት ፲፮ (አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በያዝነው ዓመት በታይግሎ አውራጃ በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከአልሸባብ ጋር ከባድ ውጊያዎችን አድርገዋል። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር ላይ የምትገኘው ስትራቴጂካዊውን የታይግሎ ወረዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ለአልሸባብ በመተው ወደ ሁዱር እና ቦቆል ሸሽተዋል። በያዝነው ወር ብቻ አልሸባብ በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እጅ የነበሩትን ሶስት ከተሞች በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ድርጅቱ አስታውቋል።
”በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአልሸባብ ታጣቂዎች መለያ ባንዲራቸውን እያውለበለቡ በከተማዋ እንብርት ውስጥ ይታያሉ። የኢትዮጵያ ወታደሮች እና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ትናንት ምሽት ላይ ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ለቀው ወጥተዋል።” ሲሉ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት የአገር ሽማግሌ መሃመድ ኑር ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የአልሸባብ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ የሆኑት አብዲይ ኣሲስ አብዱ ሙሳብ በበኩላቸው ”እኛ ስንገባ በከተማዋ የፍርሃት ድባብ ነግሷል። ማለዳ ላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደለቀቁ ወደ ታይግሎ ገብተን ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራችን ስር አውለናታል። የአልሸባብን መግለጫ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግስት በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም።
በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ አሜሶን ስር ያሉት የኬኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ እና ሌሎች የኅብረቱ ጦር አባላት ቁጥጥር ስር የነበሩ አብዛኞቹ የሶማሊያ ከተሞች በአሁኑ ወቅት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። ማክሰኞ እለት በመኪና ላይ በተጠመደ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የሶማሊያ ደኅንነት ባለስልጣንን ጨምሮ 12 ሰላማዊ ዜጎች በአልሽባብ መገደላቸው ቻናል ኒውስ ኤሲያ አክሎ ዘግቧል።