የኢትዮጵያ ጦር ከተለያዩ የሶማሊያ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቆ መጣ ተባለ

ኢሳት (ጥቅምት 14 ፥ 2009)

በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል በማዕከላዊ ሶማሊያ ከሚገኙ የተለያዩ ወታደራዊ ይዞታዎች ለሁለተኛ ጊዜ ለቆ መውጣቱ ተገለጠ።

በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑካን ስር የሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮች በማዕከላዊ ሶማሊያ ከምትገኘው ሃልጋን ከተማ ዕሁድ ጠቅልለው መውጣታቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ዙሃን ዘግበዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወታደራዊ ቁልፍ ቦታ ያደረጉትን ማኮብለል ተከትሎ የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ሃልጋን በምትሰኘው ከተማ እንደተቆጣጠረ ዘግልፍ ቱዴይ የተሰኘ ጋዜጣ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች በማዕከላዊ ሶማሊያ ከምትገኝ ሌላ ወታደራዊ ቁልፍ ይዞታ ለቀው መውጣታቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

በወቅቱ ከተመሳሳይ ወታደራዊ ይዞታ ስር ጠቅልለው የወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ጥቃት ደርሶባቸው እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ዕሁድ ረፋድ ላይ ከሃልጋን ወታደራዊ ቁልፍ ይዞታ ለቀው የወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለበርካታ ጊዜያት ተቆጣጥረው የነበሩት ጣቢያ እንዳወደሙትና በለደወይን ተብሎ ወደ ሚጠራ ግዛት ማምራታቸውን የአይን ዕማኞች ለ ዘ-ገልፍ ቱዴይ ጋዜጣ ገልጸዋል።

የሃልጋን ከተማ በታጣቂ ሃይሉ ቁጥጥር ስር መዋል በሂራን ግዛት ስር በምትገኘው የቡሎቡርዴ አስተዳደር በሚገኙ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ላይ ተከታታይ ጥቃት እንዲፈጸም አስተዋጽዖ ያደርጋል ሲሉ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስረድተዋል።

በተያዘው ወር ብቻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሞኮኮሪ እና ሌል አሊ ተብለው ከሚጠሩ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ጠቅለው መውጣታቸው ታውቋል።

ለሶማሊያ የጸጥታ ስጋት ሆኖ የሚገኘው አልሸባብ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ይዞታዎች በእጁ አስከግብቶ እንደሚገኝ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰኞ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይል በኢትዮጵያ ወታደሮች ስለተወሰደው ዕርምጃ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ድርጊቱ የጸጥታ ቁጥጥር ክፍተት ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።

ኢትዮጵያ ወደ 5ሺ የሚጠጉ የሰላም አስከባሪ ሃይሎችን በአፍሪካ ህብረ ስር በምገኘው የሰላም ልዑኩ ውስጥ አሰማርታ ብትገኝም ቁጥሩ በትክክል ያልታወቁ ተጨማሪ ሃይል በሶማሊያ አሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በሃገሪቱ ለሰባት አመት ያህል ጊዜ ያደረገችው ወታደራዊ ዘመቻ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዳስወጣትም የተለያዩ አካላት ይገልጸዋል።