ኢሳት (ህዳር 2 ፥ 2009)
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን እስላማዊ አማጺ ቡድንን ለመዋጋት ወደ ሶማሊያ የገባው የኢትዮጵያ ጦር፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአራት የሶማሊያ ስትራቲጂያዊ ከተሞች ለቆ መውጣቱ ተገለጸ። ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠር የጦር ሰራዊቷን ከሶማሊያ ማስወጣቷ፣ በአገር ውስጥ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የአፍሪካ ቀንድ ተንታኞች ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት በአሁኑ ወቅት ሶማሊያን ለቆ እየወጣ ያለበት ሁኔታ አገር ውስጥ የተፈጠረውን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ ነው ሲሉ የአልሸባብ ሃላፊዎች ለአልጀዚራ በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል። በአማራና በኦሮምያ የተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ከአልሸባብ ይልቅ ለህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ ራስ ምታት እንደሆነ የአልሸባብ መሪዎች ለአልጀዚራ ጣቢያ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ባለፉት 4 ወራት ከ 10 ወሳኝ ከተሞች ለቆ የወጣው የለምንም ማብራሪያ እንደሆነ አልጀዚራ የዜና ወኪል አርብ ዕለት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። “በሌሊት አካባቢውን ጥለው የሸሹት ህዝቡ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ስለማይፈልግ ነው” ሲሉ ሼኽ ሃሳን ያኩብ የተባሉ የጋልጋዱድ አካባቢ የአልሸባብ አስተዳዳሪ መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በበኩላቸው ጦራቸው ከሶማሊያ ከተሞች የወጣበት ምክንያት የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው ነው ይላሉ።
በሶማሊያ የተሰማራው የአሚሶም ጦር ሃይል ቃል አቀባይ የሆኑት ጆ ክበት (Joe Kibet) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣት በአሚሶም ጦር ላይ ጫና መፍጠሩን አምነዋል። የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣት ፈታኝ ቢሆንም፣ አሚሶም አሁን ባለው ሃይሉ በሶማሊያ ያለውን ሰላም ለማስከበር ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በሌላ ዜና፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቦምብ ለማፈንዳት አቅደው ነበር የተባሉ 8 የሶማሊያ ዜጎች ከሁለት እስከ 9 ኣመት በሚደርስ እስራት ተበየነባቸው። የአልሸባብ አባላት ናቸው የተባሉ 8ቱ የሶማሊያ ዜጎች፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም የአጥፍቶ መጥፋት ድርጊት ለመፈጸም አቅደዋል በሚል ክስ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።
ሶማሊያውያኑ የኢትዮጵያና የናይጀሪያ የእግር ኳስ ቡድኖች የአለም ዋንጫ እግር ኳስ ማጣሪያ በሚጫወቱበት ጥቅምት 2006 ወቅት ጥቃት ለማድረስ እቅድ እንደነበራቸው ሆኖም እቅዱ ሳይሳካ መቅረቱን አቃቤ ህግ ገልጿል። በወቅቱ ፈንጂዎች፣ የጦር መሳሪያዎችና የእጅ ቦምቦችን መያዙን የኢትዮጵያ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።