ኢሳት (ጥቅምት 22 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ የወጣው በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እንደሆነ አልሻባብ ገለጸ። ሃሳን ያቁብ የተባሉ የአልሻባብ መሪ ፣ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ በመውጣቱ አልሸባብ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል ሲሉ አፍሪካ ኒውስ ለተባለ ጋዜጣ መናገራቸው ተሰምቷል።
የአልሸባብ አስተዳዳሪ የሆኑት ሃሳን ያቆብ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ የወጡት ኢትዮጵያ በተፈጠረው የውስጥ ችግር ነው ቢሉም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የኢትዮጵያ ሰራዊትን ከሶማሊያ መውጣቱ በቅርቡ ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው፣ በደምብ የታሰበበትና ሃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ ነው እንደነበር ማስረዳታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰራዊቱና ሌሎች ወጪዎችን መክፈል አይችልም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ኢትዮጵያ ጦር ወደሶማሊያ ተመልሶ ለመግባት እንደሚችል ከዚህ በፊት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ባሳለፍነው የጥቅምት ወር ብቻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶስት ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡ ሲሆን፣ የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ሶስቱን ስፍራዎች ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ በመውጣቱ የሲቪሉ ማህበረሰብ አልሸባብ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚሰሩ የእርዳታ ሰራተኞች ህይወት አደጋ ላይ እንደጣለ ገልጿል። አልሸባብ የሶማሊያ ክልሎችን መልሶ መቆጣጠሩ በእርዳታ አሰጣጥ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።
በመንግስት ሃይሎች ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ቦታዎች አሁን በአልሸባብ እጅ ወድቀዋል ያለው ይኸው አፍሪካ ኒውስ ላይ የወጣው ዘገባ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ወታድሮች ለቀው በመውጣታቸው ለእርዳታ ስራ አስቸጋሪ የነበሩ ቦታዎች አሁን የባሰ አስከፊ ሁኔታ ገጥሟቸዋል ብለዋል።