የኢትዮጵያ ጦር ለመወረር ተዘጋጅቷል በሚል እሳቤ፣ ባላንጣ የነበሩ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመተባበር መስማማታቸው ተነገረ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)

ከሁለት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረው በመጡ ታጣቂዎች የተገደሉትን 208 ዜጎችን ለመበቀልና፣ የተጠለፉ ህጻናቱን ለማስለቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት አጸፋዊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚለውን መላ ምት ተከትሎ፣ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በጥቃቱ እርስ በዕርስ መወነጃጀላቸውን ትተው አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ሬዲዮ ታማዙጂ የተባለ የሱዳን ጣቢያ ገለጸ።

የደቡብ ሱዳን ምክትል መከላከያ ሚንስትር የሆኑት ዲቪድ ያው ያዉ እና የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ባባ ሜዳን የተባሉት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በጋምቤላ በተፈጸመው ጥቃት አንዱ ሌላውን በመክሰስ ተጠምደው እንደሰነበቱ ምንጮች ለሬዲዮ ታማጁዚ መግለጻቸው ተነግሯል።

የጥቃት አድራሾቹ ሙርሌ ጎሳ ኣባላት የሆኑት  ሁለቱም መሪዎች በቦማ ግዛት የራሳቸው የታጠቁ ተከታዮች እንዳሏቸው የተነገረ ሲሆን፣ ገዳዮቹን መሳሪያ በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግና አሰቃቂ ግድያና ጠለፋ  እንዲፈጽሙ አመራር በመስጠትም አንደኛው ሌላኛውን ሲከስ እንደነበረ ይታወቃል። የምክትል መከላከያ ሚንስትሩ ዴቪድ ያው ያው  በጋምቤላ ጥቃቱን ያደረሱት ከባባ ሜዳን ትውልድ አውራጃ የመጡ ታጣቂዎች እንደሆኑ ሲገልጹ፣ ባባ ሜዳን በበኩላቸው በጋምቤላ ክልል ጥቃት ያደረሱት የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ዴቪድ ያው ያው ተከታዮች ናቸው ብለዋል።

ሁለቱም መሪዎች ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩ ሲሆን፣  በግጭቱም ብዙ ህይወት እንደጠፋ፣ ንብረት እንደ ወደመ እና ብዙ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተነግሯል።

እንደ ሬዲዮ ታማጁዚ ዘገባ፣ በፕሬዚደንት ሳልባ ኪር ጣልቃገብነት በሁለቱ ወገኖች ዕርቅ የተፈጠረ ሲሆን፣ ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት አንድ ላይ በመሆን  በቦማ ግዛት ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት  እንደተዘጋጁም፣ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ሬዲዮ ታማዙጂ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ደቡብ ሱዳን በመግባት  የተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የደቡብ ሱዳን ሬዲዮ ታማዙጂ አክሎ ገልጿል። ወታደሮቹ ወደሱዳን ዘልቀው ገቡ የተባሉበት ቦታ በአኮቦ ግዛት፣ የቦማ ግዛት በሆነችው ፖቻላ ከተማ እና ቦማ ግዛት ጀበል አውራጃ ራድ በሚባለው አካባቢ እንደሆነ ሬዲዮ ጣቢያው መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የሙርሌ ጎሳ አባላት የሆኑና ጥቃቱን ፈጽመዋል በተባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃን ለመውሰድ ህጻናቱ የታገቱበት አካባቢ ከብቤያለሁ በአጭር ጊዜ አስለቅቃቸዋለሁ ሲል ቢቆይም እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደቡብ ሱዳን ድረስ ዘልቆ መግባቱና ከበባ መፈጸሙን የሚያመላክት ተጨባጭ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።