ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)
1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢትዮጵያ ገበሬዎች እርሻቸውን ቢያዘጋጁም፣ የሚዘሩት ዘር አጥተው ተቸግረው እንደሚገኙና የዘር እህል ባስቸኳይ እንደሚፈልጉ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት FAO አስታወቀ። እህል የሚዘራበት ወቅት ስድስት ሳምንት ብቻ ስለቀረው፣ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ለገበሬዎች ለዘር መግዣ የሚሆን የእርዳታ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሚሞክር ይኸው ድርጅት ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የአደጋ ጊዜ የቡድን መሪ የሆኑት ሮሳኔ ማርሼሲ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በሁለት ሳምንት ያቀድነውን 10 ሚሊዮን ዶላር ካላገኘን፣ አሁን ያለውን ሁኔታ የመቀየር ዕድል እናጣለን፣ ይህ ማለት ችግሩ ወደ ፊት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በመሆኑም ተመራጩ ለገበሬዎች ዘር ሰጥቶ የራሳቸውን ምግብ እራሳቸው እንዲያመርቱ ማድረግ ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
FAO በቅርቡ በድረ-ገጹ እንዳስታወቀው፣ 10.2 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በምግብ እጥረት የተጠቁ መሆናቸውን ገልጾ፣ ገበሬዎቹ የዘሩት እህል ሳይበቅል መና እንደቀረና ከብቶቻቸውም እንደሞቱባቸው በዝርዝር አስነብቧል። እንደ ፈረንጆቹ 2016/17 ዓም ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ከታዩት በላይ የከፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት አስታውቋል። አብዛኞቹ ገበሬዎች ለዘር ያስቀመጡትን እህል በረሃቡ ምክንያት አሟጠው ስለጨረሱት (ስለበሉት)፣ ለሚመጣው የሰብል ወቅት ያስቀመጡት የዘር እህል እንደሌላቸውም ታውቋል።