ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የቡናና የቅባት እህሎች ሽያጭ በመቀነሱ ምክንያት የአገሪቱ የውጭ ንግድ ሽያጭ በ7 ከመቶ መቀነሱን ብሉምበርግ የተሰኘው የዜና ምንጭ ዘገበ።
የንግድ ሚኒስቴር ዘገባን የጠቀሰው ብሉምበርግ እንደዘገበው አምና በዚህ ሰዓት የሶስት ወር የቡና ሽያጭ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ አመት ግን ከ200 ሚሊዮን ዶላር ወርዷል ብሏል።
መቀመጫው አዲስ አበባ የሆነው አክሰስ ካፒታል የተሰኘ የምርምር ቡድን ባወጣው ዘገባ፤ ባለፈው ሀምሌ ባለቀው የበጀት አመት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ጉድለት 7.5 ቢሊዮን ዶላር እንደደረስ ጠቅሷል።
መንግስት በአምስቱ አመት የልማት መርሀግብር የኢትዮጵያን የውጭና የውስጥ የንግድ ልዩነት ለመቀነስ ቃል ቢገባም፤ ኢትዮጵያ ወደውጭ በምትለከው ሸቀጥና ወደአገር ቤት በምታስገባው ሸቀጥ ዋጋ መካከል ያለው የገንዘብ ልዩነት መጠን፤ እስካለፈው ሀምሌ ድረስ ብቻ 7.5 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ታውቋል።
በዚህ አመት የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ ወደ 3.9 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ቢነገርም፤ ልክ እንደቡና ሁሉ፤ እስካሁን ባሉት ሶስት ወራት፤ የቅባት እህሎች ሽያጭ በ27 ከመቶ፤ የቆዳ ምርቶች ሽያጭ በ20 ከመቶ፤ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ሽያጭ ገቢ ደግሞ በ28 ከመቶ እንደቀነሰ ታውቋል።
የወርቅና የጫት ሽያጭ ግን በ1 እና በሁለት ከመቶ እድገት አሳይቷል።
ከዓለም በሕዝብ ብዛት 13ኛ የሆነቸው ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ከውጭ ንግድ ያገኘችው 3 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ሲሆን፤ በህዝብ ብዛቷ ከኢትዮጵያ በግማሽ የምታንሰው ኬንያ ባለፈው አመት ከውጭ ንግድ ሽያጭ ያገኘችዉ ገቢ 5.5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ታውቋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም በህዝብ ብዛት 13ኛ ትሁን እንጂ፤ በውጭ ንግድ ገቢ ግን 125 ነች። ኬንያ ደግሞ፤ 31ኛ።