የኢትዮጵያ የወርቅ ምርትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በእጅጉ በማሽቆልቆል ላይ መሆኑ  ተነገረ::

(ኢሳት ዜና -ሐምሌ 6/2009) ኢትዮጵያ ከወጭ ንግድ ጋ በተያያዘ ከፍተኛ ገቢ ከምታገኝባቸው ዘርፎች አንዱ የወርቅ ንግዷ ነው።

ከዘርፉ በአመት 350 ሚሊየን ዶላር ገቢም ታስገባለች።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ብቻ 1 ነጠብ 9 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች ብሏል ፎሩቹን ጋዜጣ በእትሙ።

ይሄ ገቢ ሲታይ ግን ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ከ19 በመቶ ወደ 10 በመቶ አሽቆልቁሏል።

የማእድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ይመለከታቸዋል ካላቸው አካላት ጋር በአዳማ የመከረበት ጉባኤም ያሳየው ይህንኑ ነው።

ጉባኤው በዋናነት በዘርፉ አሉ በሚባሉ መሰራታዊ ችግሮች፣በተጋረጡ አደጋዎችና በዘርፉ ሊወሰዱ ይገባቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኢኮኖሚው ዘርፍ የወጭና የኢንቨስትመንት ሚኒስትር ድኤታ  አቶ ታደሰ ሃይሌ ከዘርፉ የሚገኘው ምርትም ሆነ ገቢ ከሚጠበቀው በላይ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ በአንዳንድ ክልላዊ አስተዳደሮች ዜሮ ወደ ሚባል ደረጃ ወርዷል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

እነ ጋምቤላ፣ቤንሻንጉል፣ትግራይ፣ኦሮሚያንና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስትን በምሳሌነት በማንሳት።

የማእድን ኢንደስትሪዎች የግልጽነት አሰራር ተቋም በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ጥናት ከሆነ በሀገሪቱ ከሚወጣው የወርቅ ማእድን 61 በመቶ የሚሆነው በህገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወር ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሀገሪቱ በሚሊየን የሚቆጠር ገቢን እያጣች ነው ብሏል ጥናቱ።

የወርቅ ማእድንን ባማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊየን ይደርሳል።ከነዚህ አማራቾችም በየአምቱ 9 ቶን የሚደርስ የወርቅ ማእድን ይገኛል ለውጭ ገበያም ይቀርባል።

ጥናቱ እንደሚለው ግን አብዛኛው ምርት ለገበያ ሲቀርብም ህገ ወጥ በሚባል መንገድ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በአብዛኛው ምርቶቻችውን የሚያቀርቡት በህገ ወጥ መንገድ ለተሰማሩ ባላሃብቶች ነው።

ጥናቱ ችግሩ በጥቃቅን ዘርፍ ላይ በተሰማሩት ላይ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ በሚባሉት ኩባንያዎች ላይም ጎልቶ ታይቷል ነው ያለው።

በምሳሌነት ሜድሮክ ኢትዮጵያ በምርት ዘመኑ 3 ሺ 800 ኪሎ ግራም ወርቅን አምርቷል።ይሄ ደግሞ ባለፉት አምስት አምታት ሲያምርት ከነበረው የ500 ኪሎ ግራም ቅናሽ አለው።

እናም ጥናቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም በዘርፉ የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ፣ በየጊዜው ዘርፉ ያለበትን ደረጃ መፈተሽና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።

ይህንን መረጃ ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ለማእድን፣ ለነዳጅና ለተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በዘርፉ አስቸኳይ ጥናት ይደረግ ሲል ትእዛዝ ሰጧል።