ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ቅድስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ እንደዘገበው ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ትናንት ከቤኒን አቻው ጋር “ኮቶኖ” ላይ የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት በመለያየቱ ለተከታዩ ዙር ማለፉን አረጋገጠ።
የኢትዮጵያ ቡድን ከማጥቃት ይልቅ በመከላከል ላይ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን በ ዕለቱ እየጣለ የነበረው ዝናብም ጭምር የሁለቱንም ቡድኖች የጨዋታ እንቅስቃሴ ገድቦት ነበር ማለት ይቻላል።
ያም ሆኖ በሜዳቸው ላይ የሚጫወቱት ቤኒኖች በ 16ኛው ደቂቃ ላይ በሚካ ኤል ሞር አማካኝነት ጎል አስቆጥረው የበላይነቱን ያዙ።
የመጀመሪያው ግማሽ ከመጠናቀቁ በፊት አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ ቡድኑን አቻ የምታደርገዋን ጎል አስቆጠረ።
ከእረፍት መልስም ሁለቱም ቡድኖች አልፎ አልፎ ወደ ጎል ካደረጉት ሙከራ ውጭ ጠንካራ ሊባልየሚችል እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ጨዋታው አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።
በዚህ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያው ቡድን ኮኮብ ግብ አግቢ ሳላዲን ሰይድ ባለፈው ጨዋታ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክኒያት መሰለፍ አለመቻሉ፤ በኢትዮጵያ ቡድን ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አልቀረም።
ሁለቱ ቡድኖች ቀደም ሲል አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው፤ ባዶ ለባዶ መለያየታቸው ይታወሳል።
የተለያዩ የኢትዮጵያ ድረ ገፆች ቀደም ሲል እንደዘገቡት ፤ብሔራዊ ቡድናችን ወደ ቤኒን የተጓዘበት አይሮፕላን እንደተነሳ ባጋጠመው እክል ምክንያት ተመልሶ ከማረፉ በተጨማሪ፤ መንገደኞቹም ከአይሮፕላኑ ወርደው እንደነበር ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ሉሲ” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ፤የታንዛኒያ አቻውን ቡድን ዳሬሰላም ላይ 1ለ0 በማሸነፍ፣ በሚቀጥለው አመት በኢኳቶሪያል ጊኒ ለሚደረገው 8ኛው ለአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።
ባለፈው ቅዳሜ በታንዛንያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም ላይ በተደረገው በዚሁ ውድድር፤ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረችው ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ስትሆን፣ ሉሲዎቹ የዕለቱን ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ በበላይነት ተቆጣጥረውት እንደነበር ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ካሁን ቀደም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ ጨዋታ የታንዛኒያ አቻውን 2 ለ 1 በማሸነፉ፤ በድምሩ 3 ለ1 በሆነ ውጤት ነው ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው።
ሉሲዎች ካሁን ቀደም ከግብፅ አቻቸው ጋር ካይሮ ላይ ባደረጉት ጨዋታ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ቢሸነፉም፣ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የመልስ ጨዋታ 4 ለ 0 በሆነ ውጤት ግብፆችን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide