የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ወደ 4.5 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ተነገረ

ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)

በ11 በመቶ እድገትን ያስመዘግባል ተብሎ የተጠበቀው የዘንድሮው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ወደ 4.5 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ረቡዕ ይፋ አደረገ።

የመንግስት ባለስልጣናት ለተከታታይ አመታት እድገትን አሳይቷል ያሉት የኢኮኖሚ እድገት በተያዘው አመት በሁለት አህዝ እድገትን ያስመዘግባል ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይሁንና በአለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዙሪያ አዲስ ሪፖርትን ያወጣው የገንዘብ ተቋሙ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በተያዘው የፈረንጅቹ አመት 4.5 በመቶ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በተያዘው አመት 8.1 በመቶ እድገትን ያስመዘግባል ብሎ ትንበያ አስቀምጦ የነበረ ቢሆን፣ ይህንኑ ትንበያ በ 4.5 በመቶ አካባቢ ዝቅ አድርጎታል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ማስታወቁን ሜይል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪካ የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሲያሳስብ የቆየው የገንዘብ ተቋም የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በቀጣዩ አመት መሻሻልን ሊያመጣ እንደሚችልና እድገቱም ሰባት በመቶ አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ተንብዮአል።

በቅርቡ ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በድርቅና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት እስከ 10 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል መግለጻቸው ይታወሳል።

ድርቁ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የከፋ ተጽዕኖን አያሳድርም ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድሞ ተተንብዮ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በአንድ በመቶ ብቻ ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቀዋል።

ይሁንና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ እድገቱ 4.5 በመቶ ብቻ እንደሚሆን በመግለጽ፣ ጎረቤት ከንያ አይቦሪኮስት፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋልና ታንዛኒያ ከአፍሪካ ከ6-7 በመቶ የኢኮኖሚ እድገትን እንደሚያስመዘግቡ በሪፖርቱ አስፍሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት አጋጥሞት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢኮኖም እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።