የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለት 14 ቢሊየን ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለት 14 ቢሊየን ዶላር ደረሰ።

የብር ምንዛሪ ለውጡ የወጪ ንግዱ ላይ ያመጣው ለውጥ የለም ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

የንግድ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለመንግስት እና ለፓርቲ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገራት ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ብታገኝም ወደ ሃገር ውስጥ በምታስገባቸው ምርቶች ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የንግድ ሚዛን ጉድለቱ 14 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

ሃላፊው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከውጭ ሃገራት የምታስገባቸው ምርቶች ከፍተኛ በመሆናቸው ምክንያት ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ አድርጓታል።

ባለሃብቶች ፋብሪካ ገንብተው ከማምረት ይልቅ ከውጭ የተመረተ ምርት አምጥቶ በመሸጥ ቶሎ ትርፍ ለማግኘት ይሯሯጣሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል በሃገሪቱ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የውጭ ንግዱ በመቀነሱ ምክንያት የንግድ ሚዛኑ ጉድለት በከፍተኛ መጠን እንዳሰፋው ሃላፊው ገልጸዋል።

የምርት ገበያ ድርጅት ባሳለፍንው ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የግብይት መጠኑ በ40 ሺ ቶን እንደቀነሰ መዘገባችን የሚታወስ ነው።

የብር ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ መንግስት ያቀረበው ምክንያት የወጪ ንግዱን ለማበረታታት እንደሆነ ቢገለጽም በተቃራኒው የወጪ ንግዱ ከቀድሞ በባሰ አሽቆልቁሏል።

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጡን ከወጭ ንግድ መጨመር ጋር አስተሳስሮ የገለጸበት ምክንያት ውጤታማ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።

በተቃራኒው በሃገሪቱ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ለውጥ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል።

የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት 15 ነጥብ 6 በመቶ በመሆን በጥር ወር ከነበረው 2 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተጠቁሟል።

በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ፣በጥራጥሬ እህሎች፣በበርበሬና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የታየው የ50 በመቶ ጭማሪ በሸማቾች ዘንድ አስደንጋጭ ሁኔታን መፍጠሩ ተመላክቷል።