ከታሰሩት መካከል ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ኡስታዝ በድሩ ሁሴን እና ኡስታዝ ከማል ሸምሱ ይገኙበታል።
12ቱ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በምን ምክንያት እንደታሰሩ ባይታወቅም የሳውዲ አረቢያ የደህንነትና የፖሊስ አባላት በትብብር ተቀናጅተው በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።
በሳውዲ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን በዋስ ለማስፈታት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ለዋስትናም አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር መጠየቁ ተነግሯል ። የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዶቼቬሌ እንደዘገበው ኢትዮጵያውያኑ ሙስሊሞች የታሰሩት ወደ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ለሃይማኖታዊ የኡምራ ስነ-ስርአት ለመሳተፍ በተጓዙበት ወቅት ነው ተብሏል።
ታሳሪዎቹ የጸሎት ስነ- ስርአታቸውን ከጨረሱ በኋላ ባላፈው ሃሙስ ማታ በሳውዲ አረቢያ የጸጥታ ሃይሎች መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ የሙስሊም ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት በሙስሊሞች ላይ የሚደርስን በደል በመቃወማቸውና ከመንግስት ጋር ያለው ችግር በውይይት እንዲፈታ በመጠየቃቸው በሽብር ተወንጅለው ታስረው መቆየታቸው ይታወቃል።
ከአመራር አባላቱ መካከል አሁንም በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ እንዳሉ በተደጋጋሚ መዘገባችን አይዘነጋም። በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ የታሰሩት የሙስሊም ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከኢትዮጵያ ጋር በተደረገ ግንኙነት ይታሰሩ አይታሰሩ የታወቀ ነገር የለም