የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ባለፈው የፈረንጆች አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ባለፈው የፈረንጆች አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል ማስመዝገቡን አመታዊ ሪፖርቱን ያወጣው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ይፋ አደረገ።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር የ2016 አም ሪፖርቱን ለንባብ ያበቃው አለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያ ከነበራት 142ኛ ደረጃ ወደ 150ኛ ማሽቆልቆሏን አመልክቷል። ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሳውዲ አረብያ፣ ማልዲቭስ እና ኡዝቤኪስታን በአለማችን በመገናኛ ብዙሃን ነጻነታቸው ከፍተኛ ማሽቆልቆል ያስመዘገቡ አራት ሃገራት ሆነው ተፈርጀዋል።

ባለፈው የፈረንጆች አመት በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  የሃገሪቱ ዜጎች የመገናኛ ብዙሃን የመከተል መብታቸውን ከመንፈጉ በተጨማሪ ጋዜጠኞች ወከባና እንግልት እንዲደርስባቸው ማድረጉን ሪፖርቱ አብራርቷል።

ከሰባት አመት በፊት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የጸረ-ሽብርተኛ አዋጅ አሁንም ድረስ ጋዜጠኞችን ለማዋከብና ያለምንም ክስ ለእስር እንዲደዳረጉ አስተዋጽዖ አድርጎ መቀጠሉን የ2017 አም አመታዊ ሪፖርቱን ያወጣው ድርጅት ገልጿል። ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት በማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉንም ድንበር ለየሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋማት አስታውቋል።

በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸም ዛቻና ማስፈራራት እንዲሁም ክሶች በሃገሪቱ ያለው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ያለምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት 15 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ ጥቂት ሃገራት ተርታም ተመድባለች። ናሚቢያ ከ180 ሃገራት መካከል 24ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከአፍሪካ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት የተሻለች ሃገር ስትሆን ጋናና ኬፕ ቨርዴ በ26ኛና በ27ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።

ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፍንላንድ፣ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድ ደግሞ የተሻለ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ያለባቸው ሃገራት ተብለው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ባለፈው አመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁለት ሶስተኛ በሚሆነው የአአማችን ሃገራት የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ከመቼውም ጊዜ ባለይ ማሽቆልቆል ማስመዝገቡን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል። አምባገነነት ከሆኑ ሃገራት ጎን ለጎን የዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆኑ የበለጸጉ ሃገራት በመገናኛ ብዙኋን ነጻነት ላይ ያላቸው አመለካከት እየተቀየረ መምጣጡን ሪፖርቱ እንደ ፊንላድ እና አሜሪካ ያሉ ሃገራትን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።

ፊንላንድ ከአንደኛ ደረጃነት ወደ ሶስተኛ ደረጃ የወረደች ሲሆን፣ አሜሪካም በሁለት ደረጃ በማሽቆልቆል በ43ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙሃን እና ባለሙያዎች ላይ ሲያቀርቡ የቆዩት ጥቃት ሃገሪቱ ያላት ደርጃን እንድታጣ ምክንያት መሆኑ ታውቋል። ከአሜሪካ ጋር ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ሰሜን ኮሪያ ከ180 ሃገራት መካከል 180ኛ ደረጃን በመያዝ አደገኛ ሃገር ተብላ ተፈርጃለች።

ከ10 አመት በፊት በኢትዮጵያ ለግጭት ምክንያት የሆነውን ብሄራዊ ምርጫ መካሄድ ተከትሎ ከ40 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ከሃገር መሰደዳቸውንና በርካታ የህትመት ውጤቶችም እንዲዘጉ መደረጉን ሪፖርት አውስቷል።

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አካላት በሃገሪቱ ለእስር በሚዳረጉ ጋዜተኞች ጉዳይ ስጋታቸውን ሲገልፅ ቆይቷል።