ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የምርመራ ክፍል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰሩ ህንጻዎችን ባለቤቶች ለማወቅ ባደረገው ጥረት የተወሰኑትን ህንጻዎች ባለቤቶችና የወጣባቸውን ወይም የሚወጣባቸውን የገንዘብ መጠን ለማወቅ ችሎአል።
በተለምዶ ቦሌ መድሀኒአለም እየተባለ በሚጠራው ወይም ወረዳ አስራ ሰባት ውስጥ በምእረባዊያን የቤት ደረጃ የሚሰሩት ቤቶች 90 በመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ ጄኔራሎች ባለቤትነት የሚሰሩ ወይም ተሰርተው የተጠናቀቁ ናቸው።
በዚህ ስዕል የሚታየው በሶኮልላንድ ኩባንያ የሚሰራው ባለአራት ፎቅ ህንጻ የጄኔራል ወዲ አሸብር ሲሆን ምንጩን ለደህንነት ሲባል ከማንገልጸው ተቋራጭ ባገኘነው መረጃ ህንጻው በእስካሁኑ ይዘቱ 34 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል። ይሁን እንጅ ህንጻውን ለማጠናቀቅ 55 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ተችሎአል።
በስእል ሁለት ላይ የቀረበው ህንጻም እንዲሁ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 17 የሚገኝ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ታወቂ የሆነው ካልዲስ ካፌ ይገኝበታል። የህንጻው ባለቤት ኮሎኔል ታደለ ሲሆኑ ህንጻው በእስካሁ ይዘቱ 12 ሚሊዮን ብር ማውጣቱንና ሲጠናቀቅ እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ከስራ ተቋራጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በስእል ሶስት የሚታየው ግዙፍ ህንጻ ደግሞ የጄኔራል ዮሀንስ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ይዘቱ 25 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል። ህንጻው ሲጠናቀቅ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስወጣል ተብሎአል።
በስእል አራት የቀረበው መለስተኛ ህንጻ ደግሞ የጄኔራል ባጫ ደበሌ ሲሆን ህንጻው በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል። በአሁኑ ጊዜም ኤቢሲ የመኪና ክራይን የመሳሰሉ ድርጅቶች ተከራይተውታል።
በአካባቢው ያለው የተጠናከረ የጥበቃ ሁኔታ ተጨማሪ ፎቶግራፎችን ለማንሳት አዳጋች ቢሆንም፣ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት ኢንጂነሮች ከተገኘው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው፣ በቦሌ መድሀኒአለም ፊት ለፊት እና በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎን የሚሰሩት ከ4ኛ ፎቅ ጀምሮ ያሉት ህንጻዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በህወሀት ጄኔራሎች ስም፣ ወይም በቤተሰቦቻቸው የሚሰሩ ናቸው።
እነዚሁ ታማኝ ምንጮች እንደገለጡት የአብዛኞቹ ህንጻዎች ዝቅተኛ ዋጋ 45 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 95 ሚሊዮን ብር ይደርሳል።
ከስራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋራጮች እና መሀንዲሶች የቤቶችን ባለቤትነት በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ ለውጭ ሰዎች እንዳይሰጡ ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸዋል። በአካባቢው ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ወይም የተለየ ጥያቄ ለመጠየቅ የሚደፍር ሰው ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሀይሎች ተይዞ ለምርመራ ይወሰዳል።
ጄኔራል ወዲ አሸብር፣ ጄኔራል ዮሀንስና ሌሎችም ሲኒየር ጄኔራሎች ተጨማሪ ግዙፍ ህንጻዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ገንብተዋል። በመቀሌ ከተማ የሚገኙት የጄኔራሎቹ ህንጻዎች ደግሞ ለመከላከያ ሚኒስቴር ለጽህፈት ቤትና ለማሰልጠኛነት ተብሎ መከራየታቸውንና ጄኔራሎቹ በአመት በመቶ ሺ ዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያፍሱባቸው ለማወቅ ተችሎአል።
ምንም እንኳ ከህወሀት ጄኔራሎች ጋር ሲተያይ እዚህ ግባ ባይባልም፣ የኢህአዴግ ሚኒሰትሮችም ከ 1 ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን በሚጠጋ ወጪ የተለያዩ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን እያስገነቡ ነው።
አብዛኞቹ ሚኒሰትሮች በኮተቤ እና በሲኤም ሲ አካባቢዎች የሚካሄዱ የቤት ግንባታዎችን በባለቤትነት ይቆጣጠራሉ።
አዲስ ዜና ጋዜጣ በ1997ዓም የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒሰትር ገነት ዘውዴ ሶስት፣ የኢህአዴግ የፓርላማ ተወካይና የውሀ ሀብት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሺፈራው ጃርሶ፣ እንዲሁም የስራና ከተማ ልማት ሚኒሰትር የሆኑት አቶ ሀይሌ አሰግዴ ዘመናዊ ህንጻዎችን በቶዮታ ጋራጅ እና በብስራተወንጌል አካባቢዎች መገንባታቸውን በስእል አስደግፎ መዘገቡ ይታወሳል።
ከሁሉት አመት በፊት ግንቦት 7 ባካሄደው የምርመራ ጥናት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቁልፍ የአዛዥነት ቦታዎች የተቆጣጠሩት የትግራይ ተወላጆች የህወሀት ነባር ታጋዮች መሆናቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማሩትም ሆነ ከፍተኛ ምዝበራ እያካሄዱ ያሉትም እነዚሁ የህወሀት ባለስልጣናት ናቸው።
አንድ የመከላከያ አዛዥ ወርሀዊ ደሞዝ በአማካኝ 3 ሺ ብር ነው። እንደ ጄኔራል ወዲ አሸብር የመሳሰሉት ጄኔራሎች ምንም ሳይመገቡ፣ የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ ወይም እድሜ ልካቸውን ምንም አይነት ወጪ ሳያወጡ የሚከፈላቸውን ወርሀዊ የመንግስት ደሞዝ እንዳለ በባንክ ቢያስቀምጡ ፣ ከሚያስገነቡዋቸው ዘመናዊ ህንጻዎች መካከል አንዱን ህንጻ ብቻ ለማስገንባት ቢያንስ ለ150 አመት በህይወት መኖርና ሳያቋርጡ ማጠራቀም ግድ ይላቸዋል።
ከ90 በመቶ ያላነሰው ኢትዮጵያዊ በቀን ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ገቢ ይተዳደራል። ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ በሚታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ቀላል የማይባል ህዝብ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ለመመገብ ተገዶአል።
በርካታ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ምሳ መብላት አልችል ብለው በክፍል ውስጥ እንደሚወድቁ፣ በርካታ ታዳጊ ወጣቶችም አንድ ድንች ብቻ በልተው የከሰአት ትምህርት እንደሚማሩ ፣ መምህራንም ለችግረኛ ተማሪዎች በማህበር ተደራጅተው ገንዘብ በማዋጣት የምሳ መግዢ ገንዘብ እንደሚለግሱ መረጃዎችን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ለአብዛኛው ህዝብ ሲኦል፣ ለጥቂቶች ደግሞ ገነት እየሆነች መምጣቷን በርካታ ታዛቢዎች ሲገልጡ ቆይተዋል።
በቀርቡ ፋይናንሻል ኢንተግርቲ ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ በእየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ50 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እየተመዘበረ በህገወጥ መንገድ ከአገር ይወጣል። በአለፉት 7 አመታት ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ ወደ ውጭ ተልኮአል።