ኢሳት (ጥቅምት 1 ፥ 2008)
ኤል-አሊ ተብሎ በሚጠራ መንደር ለረዥም ጊዚያት ቁልፍ ነው የተባለውን ወታደራዊ ቦታ ይዘው የነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች በቅርቡ ሞኮኮሪ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ለቀው እንዲወጡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሪፖርትን አቅርቧል።
የሶማሊያ የደህንነት ባለስልጣናት አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ሃይል የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰፍረው የነበረውን ቁልፍ ወታደራዊ ጣቢያ ተከታታይ ጥቃት መፈጸማቸውን ለአለም አቀፍ መገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁልፍ ከተባሉ ቦታዎች ለቀው መውጣታቸው አልሸባብ ታጣቂ ሃይል ይዞታውን እንዲያስፋፋና እንዲያጠናክር ምክንያት መሆኑን የተለያዩ አካላት አስረድተዋል።
ኤል አሊ በምትሰኘው መንደር ከሚገኝ ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራ ጠቅልለው የወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች 70 ኪሎሜርት ዕርቀት ላይ ወደምትገኘው በለደወይን ከተማ ማቅናታቸውን አብዲርሳክ ሞአሊም አህመድ የተባሉ የደህንነት ሃላፊ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።
አልሸባብ በወታደራዊ ስፈራው ፈጽሞታል በተባለው ጥቃት የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር የሶማሊያ ባለስልጣናት ያስታወቁት ነገር የሌለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ወታደሮች ከአካባቢው የለቀቁበት ምክንያት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ኢትዮጵያ ወደ 4ሺ 400 አካባቢ ወታደሮቿን ሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ስራ አሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል። ይሁንና ቁጥራቸው ያልታወቀ ተጨማሪ ወታደሮችም በተናጥል ከአልሸባብ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መሆናቸው የነገራል።
ወደ 22ሺ የሚጠጉ የአህጉሪቱ ወታደሮች በሃገሪቱ በመሰማራት ሰላምና መረጋጋትን በሶማሊያ ለማስመለስ ጥረት ቢያደርጉም አልሸባብ ታጣቂ ሃይል አሁንም ድረስ የጸጥታ ስጋት መሆኑን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።