ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
በሶማሊያ ታጣቂ ሃይል ቁጥጥር ስር የሚገኘው የጁባላንድ ግዛትን መልሶ ለመያዝ የኢትዮጵያ ወታደሮች ውጊያ መጀመራቸውን የሶማሊያ ባለስልጣናት ማክሰኞ ገለጡ።
እሁድ ወደ ዋና ከተማዋ ኪስማዩ ከደረሱት ወታደሮች በተጨማሪም ወደ 300 የሚጠጉ ወታደሮች በግዛቲቱ ስር በምትገኘው ዋርዴር አካባቢ መድረሳቸውንም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች መልሶ ለመያዝ ጥረት እያደረጉበት ያለው አካባቢ ባለፈው አመት በሴራሊዮን ሰላም አስከባሪ ሃይል ስር የነበረ ሲሆን፣ የሴራሊዮንን ወታደሮች በሃገራቸው ተቀስቅሶ የነበረን የኢቦላ በሽታ የመከላከል ዘመቻ ለማገዝ ስፍራውን ለቀው እንደወጡ የሶማሊያ ባለስልጣናት ገልጽዋል።
አካባቢውን ለቆ ለመውጣትም ለቀናቶች የሚቆይ ውጊያ ሊካሄድ እንደሚችል ወታደራዊ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ማክሰኞ በተጀመረው ውጊያም በታጣቂ ሃይሉ ላይ ሆነም በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰ ጉዳት የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለዚሁ ዘመቻ በርካታ ወታደሮችንና መሳሪያዎችን ማሰማራቷ ታውቋል።
ከሰባት አመት በፊት ጀምሮ ወታደሮቿን ወደሶማሊያ አሰማርታ የምትገኘው ኢትዮጵያ በታጣቂ ሃይሉ ላይ በምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ወታደሮቿን እንዳጣች ይነገራል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ለሰባት አመት ያህል ጊዜ ስለደረሰበት ጉዳት እስከአሁን ድረስ የሰጠው ዝርዘር መረጃ የለም።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ወደ 20ሺ የሚጠጋ ሰላም አስከባሪ ሃይልን በሶማሊያ አሰማርቶ ቢገኝም፣ አልሻባብ የተሰኘው ታጣቂ ሃይል አሁንም ድረስ የሃገሪቱን የጸጥታ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የፖለቲካ ተንታኞች አስረድተዋል።
ኢትዮጵያም በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ስር እንዲሳተፉ ካደረገችው ከ 4ሺ አካባቢ ሰራዊት በተጨማሪ በርካታ ወታደሮችን በተናጠል በማሰማራት ወታደራዊ ዕርምጃ እየወሰደች ይገኛል።