ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በያዝነው አመት ኢትዮጵያ ለውጭ ያቀረበችው ቡና በግማሽ ቀንሶአል። ባለፉት ስምንት ወራት የተገኘው የቡና ኤክስፖርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ 447 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ቡና ላይ ከአዘገጃጀት ጉድለት አንፃር የተከሰተን የጥራት ችግር እንዲሁም በላኪዎች የሚታየው ተደጋጋሚ ማጭበርበርን ተከትሎ ቡና ገዥ አገሮች ሙሉ በሙሉ ፊታቸውን ወደ ብራዚል ማዞራቸው እየተገለጠ ነው፣ ዋና ዋና የሚባሉት ቡና ተቀባይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ይዛ የቆየችውን ስሟን ልታጣ ትችላለች በማለት አስጠንቅቀዋል።
በርካታ ነጋዴዎች መንግሥት በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው አሳሪ መመሪያዎች ምክንያት ከገዥዎቻቸው ጋር የገቡትን ቃል ሊጠብቁ ስላልቻሉ ከገበያ መውጣታቸው ተገልጿል።
በዚህ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከቡና ኤክስፖርት 1.1 ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፤ የ2004 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው ከቡና የወጭ ንግድ የተገኘው 505.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
መንግሥት ከ32 ዓይነት የኤክስፖርት ምርቶች እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት አገኛለሁ ብሎ ያቀደው አራት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ እየቀረው ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልሞላም፡፡
ለዚህም እቅድ አለመሳካት ዋነኛው ምክንያት የቡና ኤክስፖርት በግማሽ መውደቁ እንደሆነ ተመልክቷል።
መንግስት የቡናን መውደቅ ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ገቢውን ከጫት፣ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ለስራ የደረሱና ያልደረሱ ወጣት ሴቶችን ወደ አረብ አገራት በተለይም ወደ ሳውዲ አረቢአ በመላክ በቡና ያጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማካካስ እየተሯሯጠ ነው። መንግስት በዚህ አመት እስከ 100 ሺ የሚደርሱ ልጀገረዶችን ወደ አረብ አገራት በመላክ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሰፊ እቅድ ዘርግቷል። አንዳንድ ወገኖች ይህ የመንግስት እቅድ ባርነትን የሚያስፋፋና ስነምግባር የጎደለው ነው ሲሉ ይተቻሉ። ይሁን እንጅ መንግስት ከቡና ቀጥሎ አቋራጭ የገንዘብ ምንጭ ማግኛ አድርጎ የወሰደው የሰው ጉልበት ሽያጭ ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide