ጥር ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በፍሬው አበበ ላይ ክስ የመሰረቱት ዲያቆን ዳን ኤል ክብረት “ አቡነ ማትያስ ፣ ለመንግስት የደህንነት፣ ለቤተክርስቲያን ደግሞ የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ በቤተክርስቲያኒቱ ስላለው ብልሹ አሠራርና ሙስና በግል ድረ ገጹ የጻፈውን ጽሁፍ ጋዜጣው ላይ በማተሙ ነው።
በሁኔታው የተበሳጩት አባ ማትያስ በጋዜጠኛው ላይ የወንጀል ክስ ከመመሥረታቸውም ባሻገር የ100 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላቸውም የፍትሐ ብሔር ክስ ከፍተው ነበር።
ጋዜጠኛው በተደጋጋሚ በፍርድ ቤት ሲመላለስ በቆየባቸው ባለፉት ወራት ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ ለልጁ ይቅርታ እንዲያደርጉለትና ጉዳዩ በእርቅና በይቅርታ እንዲፈታ በሽማግሌዎች የቀረቡላቸውን የተማጽኖ ጥያቄዎች አሻፈረኝ በማለት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አማካይነት የክሱን ሂደት ቀጥለውበት ቆይተዋል።
ይሁንና ላለፉት ስድስት ወራት የክሱን ሂደት ሲከታተል የቆየው ፍርድ ቤት፣ በዛሬው ዕለት ጋዜጠኛውን-በፓትርያርኩ ከተመሰረተበት ክስ በነጻ አሰናብቶታል።
ስለ እርቅ፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ፍቅር እንዲያስተምሩ በፓትርያርክነት የተሾሙት አቡነ ማትያስ፣ የሰውን ጽሁፍ ላተመ ለአንድ ጋዜጠኛ የይቅርታ ልብ ማጣታቸው ሲያስገርማቸው የቆዩ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምዕመናን፤ በዛሬው ዕለት ጋዜጠኛው በፍርድ ቤት ነጻ መኾኑን ተከትሎ “ አቡኑ ምን ይሰማቸው ይሆን?” በማለት ጠይቀዋል።